በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የሶማሊያ ፕሬዚዳንት አዲስ ጠቅላይ ሚኒስትር ሾሙ


አዲስ ተመራጩ ጠቅላይ ሚኒስትር ሀምዛ አብዲ ባሬ
አዲስ ተመራጩ ጠቅላይ ሚኒስትር ሀምዛ አብዲ ባሬ

የሶማሊያ ፕሬዚዳንት ሀሰን ሼክ መሀሙድ የሀገሪቱ የህግ መምሪያ ምክር ቤት አባል የሆኑትን ሀምዛ አብዲ ባሬን ጠቅላይ ሚኒስትር እንዲሆኑ መርጠዋቸዋል።

ፕሬዚዳንቱ ዛሬ በቤተ መንግሥቱ በተካሄደ ሥነ ስርዓት ሹመቱን ይፋ ባደረጉበት ንግግራቸው "ሀምዛ ያላቸውን ዕውቀት፣ ተሞክሮአቸውን እና ብቃታቸውን በመገምገም ሶማሊያ አሁን ባለችበት አዲስ ምዕራፍ ይህን አዲስ ኃላፊነት በብቃት ለመወጣት የሚሉ ትክክለኛው ሰው ናቸው ከሚል ድምዳሜ ላይ ደርሻለሁ" ብለዋል።

ፓርላማው የጠቅላይ ሚኒስትሩን ሹመት ፈጥኖ እንዲያጸድቅም ፕሬዚዳንቱ ጠይቀዋል። እርሳቸውንም ፀጥታን፥ የድርቅ አደጋ ምላሽን፣ ዕርቀ ሰላም፣ የማኅበረሰብ ዕድገት እና የአየር ንብረት ነክ ችግሮች በመሳሰሉ ቅድሚያ ትኩረት የሚገባቸው ጉዳዮች ላይ ፈጥነው ሥራ እንዲጀምሩ ጠይቀዋቸዋል። "የሶማሊያን ህዝብ ይንከባከቡ፣ የውጭ ግንኙነቷንም ያዳብሩ" ሲሉ አሳስበዋቸዋል።

ሀምዛ አብዲ ባሬ በበኩላቸው ፕሬዚዳንቱ አምነውባቸው ስለመረጧቸው መደሰታቸውን ገልጸዋል። ሶማሊያን እና ህዝቧን ካሉባት ፈተናዎች ለማውጣት ብቃት ያለው መንግሥት አቋቁማለሁ ብለዋል።

ሃምዛ ባለፈው ታህሳስ ለመጀመሪያ ግዜ የተመረጡ የመምሪያው ምክር ቤት አባል ሲሆኑ ቀደም ብሎም የጁባላንድ ክልል የምርጫ ኮሚሽን ሊቀ መንበር እንደነበሩ ታውቋል።

የአርባ ስምንት ዓመቱ ሀምዛ የፕሬዚዳንቱ የሰላም እና የልማት ፓርቲ አባል ሲሆኑ እአአ ከ2011 እስከ 2017 የፓርቲው ዋና ጸኃፊ ሆነው አገልግለዋል። ከዚያ በፊት የህገ መንግሥታዊ ጉዳዮች ሚኒስቴር እና የፌዴራል መንግሥቱ ከፍተኛ አማካሪ ነበሩ።

ለበርካታ ዓመታት ሞቃዲሾ እና ኪስማዮ ውስጥ ያስተማሩት አዲስ ተመራጩ ጠቅላይ ሚኒስትር የኪስማዮ ዩኒቨርስቲ መስራች ናቸው።

XS
SM
MD
LG