በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ዩናይትድ ስቴትስ ከዩክሬን እህል ለማውጣትና ለዓለም ገበያ ለማቅረብ ከሃገሪቱ ጋራ እየሰራች ነው


ዩናይትድ ስቴትስ ከዩክሬን እህል ለማውጣትና ለዓለም ገበያ ለማቅረብ ከሃገሪቱ ጋራ እየሰራች ነው
please wait

No media source currently available

0:00 0:04:06 0:00

በዓለም በተለይም በአፍሪካ እያደገ የመጣውን የረሃብ ቀውስ ለመግታት ወደ ሦስት ሚሊዮን ቶን የሚጠጋ ሰብል ከዩክሬን ለማውጣት የአሜሪካ ባለሥልጣናት ከሀገሪቱ መሪዎች ጋር እየመከሩ ነው።

ዩክሬን ከሩሲያ ወረራ በፊት ወደ ስድስት ሚሊዮን ቶን እህል በየወሩ ለዓለም ገበያ ታቀርብ ነበር። ጦርነቱን ተከትሎ ሩሲያ የጥቁር ባህርን መተላለፊያ በመዝጋቷ ግን 400 ሚሊዮን ሰዎችን ሊመግብ የሚችል ሰብል ዩክሬን ዉስጥ ተቀምጦ ቀርቷል።

ዩክሬን ምርቷን ለውጪ ገበያ ማቅረብ ባለመቻሏ በሚሊዮን ቶን የሚቆጠር እህል እጇ ላይ ይገኛል። ሀገሪቱ በሩሲያ መወረሯን ተከትሎ ዓለም በምግብ እጥረትና እያሻቀበ በመጣ የሰብል ዋጋ አየተቸገረ ነው።

በአሜሪካ የውጪ ጉዳይ ም/ቤት የማዕቀብ አስተባባሪ የሆኑት ጂም ኦብራይን እንደሚሉት ሚሊዮኖችን ለመመገብ የሚበቃ እህል አለ። ነገር ግን የሩሲያ ወረራ ሰብሉን ከዩክሬን ለማስወጣት አዳጋች አድርጉታል።

“ሃያ ሚሊዮን የሚጠጋ እህል ክዩክሬን ለመውጣት ቁጭ ብሎ እየጠበቀ ነው። በሰላሙ ግዜ ቢሆን ይህ እህል ገበያ ላይ ነበር የሚገኘው። በዓለም የምግብ ዋስትና በብዙ ምክንያቶች አደጋ ውስጥ ነው። ይህ 20 ሚሊዮን እህል ከ 200 እስከ 400 ሚሊዮን ሰዎችን ሊመግብ የሚችል ሲሆን የሩሲያን ውሳኔ የጠብቃል” ብለዋል ኦብራይን።

ሩሲያ እና ዩክሬን የዓለም የዳቦ ቅርጫቶች ናቸው። ሁለቱ ሃገሮች ብቻ ዓለም ከሚያስፈልገው ሰብል አንድ አራተኛውን ለገበያ ያቀርባሉ።

ባለሞያዎች እንደሚሉት የሰብል ግዢያቸውን በዩክሬን ላይ ጥገኛ ያደረጉ ሀገሮች በከፍተኛ የምግብ ዋጋ እና የአቅርቦት ችግር እየተሰቃዩ ነው።

የሴኔጋሉ ፕሬዚዳንትና የወቅቱ የአፍሪካ አንድነት ሊቀመንበር ማኪ ሳል ዩክሬን ኦዴሳ የተባልውን ወደብ ከፈንጂ በማጽዳት እህል ወደ ውጪ ለመላክ እንዲውል እንድታደርግ ባለፈው ሐሙስ ጠይቀዋል።

ማኪ ሳል ፍራንስ 24 ሬዲዮ እና ፍራንስ ኢንተርናሽናል ከተሰኙ መገናኛ ብዙሃን ጋር ባደረጉት ቆይታ አፍሪካ ከዩክሬን ስንዴ የማታገኝ ከሆነ አህጉሪቱ አለመረጋጋትን ሊፈጥር የሚችል ረሃብ ይገጥማታል ብለዋል።

“ሩሲያ ዩክሬንን ለራሷም ሆነ ለዓለም ምግብ የማምረት አቅሟን ቀንሳባታለች” ያሉት ኦብራይን “ዩክሬን ወደ 6 ሚሊዩም ቶን የሚጠጋ ሰብል በየወሩ ለዓለም ገበያ ታቀርብ ነበር። ይህ አሁን ቆሟል። ሩሲያ 30 በመቶ የሚጠጋ የዩክሬንን ሰብል ማምረቻን ይዛለች። ምግብ የማከማቻና የማደራጃ ማዕከላትንም ደብድባለች” ሲሉ ተደምጠዋል።

የምግብና የነዳጅ ዋጋ መጨመር፥ እንዲሁም ባለፉት 40 ዓመታት ታይቶ የማይታወቅ ድርቅ በምስራቅ አፍሪካ በመከሰቱ 20 ሚሊዮን የሚጠጋ ሕዝብ ከረሃብ ጋር ተፋጦ ይገኛል።

ምዕራብ አፍሪካና የሳህል ቀጠናም ምግብ ከሩሲያና ዩክሬን አስመጪ በመሆናቸው ሳቢያ ተመሳሳይ ዕጣ ገጥሟቸዋል።

የዓለም የምግብ ዋስትና የአሜሪካ ልዩ ልዑክ የሆኑት ዶ/ር ኬሪ ፋውለር እንደሚሉት በአፍሪካ ረሃብን ለመቀንስ ሀገራቸው እየረዳች ነው።

“በአጣዳፊ ሁኔታ ውስጥ የሰብአዊ ድጋፍ ለማድረግ ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ላይ ነን። ዘላቂ መፍትሄዎችንም በመሻት ላይ ነን። የአሜሪካ ዓለም አቀፍ ልማት ወኪል የሚያካሂደው ፊድ ዘ ፊውቸር (Feed the Future) የተሰኘው ልዩ ፕሮግራም በደርዘን የሚቆጠሩ ሃገሮች ውስጥ እየተከናወነ ይገኛል። ከዚህ ውስጥ ስምንቱ አፍሪካ ውስጥ የመስሉኛል። ይህን ፕሮግራም ለማስፋፋት ዕቅድ አለን” ብለዋል ዶ/ር ኬሪ ፋውለር።

ሩሲያ የዩክሬንን እህል ሰርቃ ለወዳጅ ሀገሮ እየሸጠች ነው ስትል አሜሪካ ትከሳለች።

ሳሙኤል ንያንዴሞ በናይሮቢ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ መምዕር ናቸው። ሩሲያ ከዩክሬን የሰረቀችውን ሰብል አፍሪካ አትገዛም፥ ሌሎች የተሻሉ የገበያ አማራጮችን ታማትራለች ይላሉ።

“ከዩክሬን የተሰረቀ ሰብል ከሩሲያ የሚገዛ የአፍሪካ ሀገር ያለ አይመስለኝም። የተሻሉ የገበያ አማርጮችን በተለይም ተመሳሳይ ሰብል ከሚያመርቱት ከአርጄንቲናና ከላቲን አሜሪካ የመግዛት አማራጮችን ትመለከታለች። ከሁሉ የተሻለው አማራጭ ግን ሩሲያና ዩክሬን በጠረጴዛ ዙሪያ ተቀምጠው ችግሩን በዲፕሎማሲያዊ መንገድ ቢፈቱት ነው።”

ከዩክሬይን ጎረቤቶችና ከአውሮፓ ኅብረት ጋር በመተባበር ከሀገሪቱ የሚቻለውን መጠን ያህል እህል ለማውጣት እንዲሁም በኦዴሳ ወደብ ላይ የተጣለውን እገዳ ለማንሳት እየሰሩ እንደሆነ የአሜሪካ ባለሥልጣናት ይናገራሉ።

XS
SM
MD
LG