በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በድንገት ሕይወቱ ያለፈው ድምፃዊ ዳዊት ነጋ አስክሬን እንዲመረመር ቤተሰቦቹ ጠየቁ


ድምፃዊ ዳዊት ነጋ
ድምፃዊ ዳዊት ነጋ

ታዋቂው የትግርኛ ሙዚቃ ድምፃዊ ዳዊት ነጋ በድንገት ከዚህ ዓለም በሞት መለየት ያስደነገጣቸው ቤተሰቦቹ፤ በሦስት ቀናት ህመም ለሞት ያበቃው ምክንያት ምን እንደሆነ እንዲታወቅላቸው በጠየቁት መሰረት የአስክሬን ምርመራ መደረጉን እና ውጤቱም ከአንድ ወር በኋላ እንደሚገለፅ እንደተነገራቸው የሥራ ባለደረባው ለአሜሪካ ድምፅ ገለፀ።

የድምፃዊ ዳዊት ነጋ ሕይወት ማለፍ የተሰማው ትናንት እሑድ ከምሽቱ አንድ ሰዓት ላይ ነበር፡፡ ድምፃዊ ባለፈው ሳምንት የህመም ስሜት እንደነበረበት ሲናገር መቆየቱን እና አርብ ዕለት ግን በባለቤቱ ግፊት ወደ አዲስ ህይወት ሆስፒታል መግባቱን አብሮ አደግ ጓደኛው አቶ አዲስ ኃይለስላሰ ገልጿል፡፡

ድምፃዊው እየታከመ በነበረበት ወቅት ህመሙ እየተባባሰ ሄዶ መተንፈስ ስላቃተው ወደ ፅኑ ህሙማን መታከሚያ ክፍል ገብቶ እንደነበርም ጓደኛው ለአሜሪካ ድምፅ ተናግሯል።

“አተነፋፈሱ እየወረደ በመሄዱ አዲስ መድሃኒት እንድንገዛ ድምፃዊ የሆስፒታሉ ሐኪሞች ነገሩን” የሚለው አቶ አዲስ ኃይለስላሴ መድሐኒቱን በፍለጋ ሜክሲኮ አካባቢ አግኝተው ገዝተው ሲመለሱ ማረፉን ገልፀዋል፡፡

አሟሟቱ ድንገተኛ በመሆኑም የአስከሬን ይመርመርልን ጥያቄ ከቤተሰቦችና ከወዳጆቹ በመቅረቡ በዛሬው ዕለት (ሰኞ) የአስከሬን ምርመራ ተደርጓል፡፡ የምርመራ ውጤቱም ከአንድ ወር በኋላ ይገለፃል ተብሏል፡፡

በ1979 ዓ.ም መጨረሻ ላይ በመቐለ ከተማ ነው የተወለደው ድምጻዊ ዳዊት ነጋ ወላጆቹ በልጅነቱ ነበር በሞት የተለዩት፡፡ አባቱ ቀደም ብለው ያረፉ ሲሆን፣ እናቱ ደግሞ በዘጠኝ ዓመቱ ተለይተውታል፡፡ በዚህ ምክንያት ዳዊት በዘመድ ቤት ተጠግቶ ማደጉንና ብዙ ችግር ሲደርስበት እንደነበር በህይወት እያለ በሰጣቸው ቃለ ምልልሶች ተናግሯል፡፡ ከልጅነቱ ጀምሮ ራሱን ለመምራት ሲጋራ፣ ማስቲካና እንቁላል በየመንገዱ እየሸጠ ነበር ያደገው፡፡

ትልቅ ሙዚቀኛ የመሆን ህልም እንደነበረው የሚያስታውሱት አቶ አዲስ፣ መቐለ ወደነበረው ሰርከስ ትግራይ የሙዚቃ ቡድን ሙዚቀኛ ለመሆን ማመልከቱንና እነሱም በድምፃዊነት ባይቀበሉትም፣ እዛው በሰርከስ ትግራይ በከበሮ ተጫዋችነት ሥራ እንደጀመረ ነግረውናል፡፡

በዚህ ሒደት ወደ ሙዚቃው ዓለም ከተቀላቀለ በኋላ የትግርኛ ባህላዊ ዘፈን መሥራት ጀመረ፡፡ ከዛም እንደ “ዳእመና”፣ “ከም ገልገለገ መስቀል”፣ “ባባ ኢለን”፣ “ወዛመይ”፣ “ዘዊደሮ” የሚሉትን ጨምሮ

ከ30 በላይ ሙዚቃዎችን ሰርቷል፡፡ አሁንም ሌላ ሙዚቃ ለማሳተም በዝግጅት ላይ እንደነበረ ለማወቅ ተችሏል፡፡ ዳዊት ነጋ ባለትዳርና የአምስት ዓመት ወንድ ልጅ አባት ነበር፡፡

XS
SM
MD
LG