ታስረው የነበሩት የቀድሞው የአማራ ክልል ልዩ ኃይል አዛዥ ብሪጋዲየር ጄነራል ተፈራ ማሞ ዛሬ በዋስ መለቀቃቸውን ጠበቃቸው ለአሜሪካ ድምፅ ገልፀዋል።
ጄነራሉ የተያዙት "ህገ መንግሥቱን በኃይል ለመናድ መሞከር" በሚል ወንጀል ተጠርጥረው እንደሆነ ጠበቃቸው አስታውሰዋል።
የአማራ ክልል ልዩ ኃይል የቀድሞው አዛዥ ብሪጋዲየር ጀነራል ተፈራ ማሞ በዋስ እንዲለቀሱ የወሰነው የዋስትና አቤቱታውን ከትናንት ጀምሮ ሲመለከት የቆየው ዛሬ ባህር ዳር ላይ ያስቻለው የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ነው።
ጠበቃቸው አቶ ሸጋው አለበል ለአሜሪካ ድምፅ በሰጡት ቃል ፍርድ ቤቱ ጄነራሉን የለቀቀው በ30 ሺ ብር ዋስትና መሆኑን ገልፀዋል።
አቃቤ ህግ ባሰማው አቤቱታ "የተከሰሱበት የሽብር ወንጀል በመሆኑ የዋስትና መብት አያሰጥም" ሲል መከራከሩንም አቶ ሸጋው ገልፀዋል።
ፍርድ ቤቱ ጉዳዩን በይደር ካቆየ በኋላ "የሽብር ወንጀልም ቢሆን የዋስትና መብት አያስከለክልም' በማለት በ30 ሺህ ብር ዋስትና እንዲለቀቁ ወስኗል።
"ህግ መንግሥቱን በኃይል ለመናድ መሞከር" በሚል ተጠርጥረው የተያዙት የቀድሞው የልዩ ኃይል አዛዥ እሥር ቤት ውስጥ ለ25 ቀናት መቆየታቸውን አቶ ሸጋው አመልክተዋል።
በቀድሞው የኢህአዴግ አስተዳደር ወቅትም በመፈንቅለ መንግሥት ወንጀል ተጠርጥረው ለ9 ዓመታት የታሠሩት ብሪጋዲየር ጀነራል ተፈራ ማሞ ያኔ የተለቀቁት በ2010 ዓመተ ምህረቱ የመንግሥት ለውጥ ሰሞን ነበር።
በኋላም በክልሉ ልዩ ኃይል አዛዥነት ለጥቂት ወራት ካገለገሉ በኋላ ከሰኔ 15/2011 የአማራ ክልል ከፍተኛ አመራር አባላት ግድያ ጋር በተያያዘ ተጠርጥረው ለ6 ወራት ታስረው መፈታታቸውም ይታወሳል።