በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ኢትዮጵያ በአፍሪካ ዋንጫ የማጣርያ ጨዋታ ግብፅን 2 - 0 አሸነፈች


ፎቶ ፋይል፦ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን
ፎቶ ፋይል፦ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የግብፅ አቻውን 2 - 0 በማሸነፍ በማጣሪያው የመጀመሪያውን ሦስት ነጥብ አግኝቷል።

ባለፈው እሁድ ከማላዊ አቻው ጋር የአፍሪካ ዋንጫ የምድብ ማጣሪያ የመጀመሪያ ጨዋታውን በሊሎንጉዌ ያደረገው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የማጣሪያ ውድድሩን 2 ለ 1 በመሸነፍ ቢጀምርም በሁለተኛ ጨዋታው ጣፋጭ ድል አስመዝግቧል፡፡

ብሔራዊ ቡድኑ በዚያው በማላዊ ከግብፅ ጋር ዛሬ ባደረገው ጨዋታ ለቡድኑ ሁለቱን ጎሎች ያስቆጠሩት ዳዋ ሆጤሳ እና ሽመልስ በቀለ ሲሆኑ ጎሎቹ የተቆጠሩት በመጀመሪያው አጋማሽ ነው።

ግብፅ ከእረፍት መልስ ተጭና ለመጫወት ጥረት ብታደርግም የውጤት ለውጥ ማምጣት ሳትችል፣ ጨዋታው በኢትዮጵያ 2 ለ 0 አሸናፊነት ተጠናቋል።

በኮትዲቯር አዘጋጅነት ለሚካሄደው ለቀጣዩ የአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ በምድብ አራት ከግብፅ፣ ማላዊ እና ጊኒ ጋር የተደለደለችው ኢትዮጵያ፣ የካፍን ዝቅተኛ መስፈርት የሚያሟላ ስታዲየም የሌላት በመሆኑ ነው በሜዳዋ ታደርግ የነበረውን የዛሬውን ጨዋታ ከሜዳዋ ውጭ ለማድረግ የተገደደችው።

ኢትዮጵያ ዛሬ ግብፅን ማሸነፏን ተከትሎ ምድብ አራትን በግብ ብልጫ መምራት ጀምራለች።

ዛሬ በተደረገ ሌላ የምድብ አራት ጨዋታ ጊኒ ማላዊን 1 - 0 ያሸነፈች ሲሆን፣ ኢትዮጵያን ጨምሮ በምድቡ የሚገኙት አራቱም ሀገራት ካደረጓቸው ሁለት ጨዋታዎች አንዱን በማሸነፍ እኩል ሦስት ነጥብ አላቸው።

ኢትዮጵያ ቀጣይ የምድብ ማጣሪያ ጨዋታዋን ከጊኒ ጋር የምታደርግ ይሆናል።

XS
SM
MD
LG