የዩክሬይን እና የሩሲያ ኃይሎች ዛሬ ሰኞ በምስራቅ ዩክሬይኗ ሲቪዬሮዳኔትስክ ከተማ ፣ ከባድ የጎዳና ላይ ውጊያ እያካሄዱ መሆኑ ሲገለጽ፣ የዩክሬን ፕሬዚዳንት ቮሎዶሚር ዘለንስኪ፣ የሩሲያ ወታደሮች በስተደቡብ ምስራቅ የምትገኘውን ዛፖርዚያ ከተማ ለመያዝ እያሰቡ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
የከተማዪቱ አስተዳደር ኦሊክሳንደር ስትርዩክ በቴሌቪዥን እንደተናገሩት በሲቪዬሮዳኔትስክ ያለው ሁኔታ “ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተለዋወጠ ነው፡፡”
የዩክሬን ፕሬዚዳንት ቮሎድሚር ዘለንስኪም የዩክሬን ኃይሎች ከተማይቱን ለመቆጣጠር “ሁሉም ዕድል” ነበሯቸው ብለዋል፡፡ የዘለንስኪ አስተያየት የመጣው የሉሃንስክ ግዛት አገረ ገዥ ሴርሂ ሃይዳይ ዩክሬን ይዞታዎችዋን ማጣቷን ከገለጹ በኋላ ነበር፡፡
ሃይዳይ “ተፋላሚዎቻችን ለተወሰነ ጊዜ መልሶ ማጥቃት ችለው ነበር፡፡ የከተማውን ከፊል ያህል ነጻ አውጥተውም ነበር፡፡ ይሁን እንጂ አሁን ሁኔታዎች እንደገና ተመልሰው ለኛ የከፉ ሆነዋል” ብለዋል፡፡
ሩሲያና ዩክሬን፣ ሁለቱም አንዳቸው ባንዳቸው ላይ ከባድ ጉዳት ማድረሳቸውን ይገልጻሉ፡፡
ዘለንስኪ ትናንት ሰኞ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ የሩሲያ ወታደሮች ወደ ማዕከላዊ የአገሪቱ ክፍል ለመቃረብ የምታስችላቸውንና፣ በስተደቡብ ምስራቅ በኩል የምትገኘው ዛፖርዚያን ለመያዝ፣ እያሰቡ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ዘለነስኪ በመግለጫቸው “ጠላት የሚፈልገው የዛፖርዚያ ከተማን ለመቆጣጠር ነው” ብለዋል፡፡ከተማዪቱ የኢንደስትሪ መናኻሪያ ስትሆን ከጦርነቱ በፊት ከ700 ሺህ በላይ ነዋሪዎች ነበሯት፡፡
የዩክሬን መሪ በዚሁ መግለጫቸው የብሪታኒያው ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን “የተጠናከሩ አዳዲስ የጦር መሳሪያዎች የተካተቱበትን ድጋፍ” የሚሰጧቸው መሆኑን እንዳረጋገጡላቸው ተናግረዋል፡፡ ሁለቱ አገሮች የምግብ ቀውስ እንዳይደርስ ለመከላከል የዩክሬን ወደቦችን በማስከፈት በሚያስችላቸው መንገድ ላይ መነጋገራቸውም ተመልክቷል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ ብሪታኒያ ዒላማቸውን እስከ 80 ኪሎ ሜትር ሊመቱ የሚችሉ “ኤም 270” የተባሉ፣ በአንድ ጊዜ በርካታ ሮኬቶችን አስወንጫፊ መሳሪያዎችን ለዩክሬን እየላከች መሆንዋን አስታውቃለች፡፡
የብሪታኒያው ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን “የሩሲያ የረጅም ርቀት መድፎች፣ ከተሞችን እያወደሙ ሰላማዊ ሰዎችን ሲገድሉ ዝም ብለን ቆመን ልንመለከት አንችልም” ብለዋል፡፡
የዩክሬን ፕሬዚዳንት ዘለነስኪም ትናንት ሰኞ ባሰሙት፣ በየምሽቱ በሚያስተላልፉት የቪዲዮ መልዕክታቸው “ዝግጁነታችንና የሚያስፈልጉንን ነገሮች ሁሉ ተረድተው የሰዎቻችንን ህይወት ለመታደግ፣ ዩክሬን የሚያስፈልጋትን ትክክለኛ የጦር መሳሪያ ድጋፍ ስላደረጉልን፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰንን አመሰግናለሁ፡፡” ብለዋል፡፡
የብሪታኒያው መከላከያ ሚኒስትር ቤን ዋለስ፣ ለዩክሬን የሚሰጠው እርዳታ ሩሲያ ስልቶቿን በለወጠች ቁጥር አብሮ መለዋወጥ አለበት ብለዋል፡፡ እነዚህ አዳዲስ የሮኬት መሳሪያዎች “ዩክሬናውያን ወዳጆቻችን፣ የፑቲን ኃይሎች፣ ያለምንም ልዩነት ከተሞችን ለመደምሰስ ከሚጠቀሙባቸውና፣ ለጭካኔ ከሚያውሏቸው ከእነዚያ ረጅም ርቀት ከሚጓዙ መድፎች እንዲከላከሉ ያስችላቸዋል” ሲሉ ተናግረዋል፡፡
የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ምዕራባውያን ለዩክሬን የረጅም ርቀት ሚሳዬል መሳሪያዎች ለመስጠት ባላቸው ዕቅድ የሚገፉበት ከሆነ "እስከዛሬ ያላጠቃናቸውን ዒላማዎች" እናጠቃለን ሲሉ አስጠንቅቀዋል፡፡
የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ለኪየቭ መንግሥት ለአዳዲስ ዘመናዊ የጦር መሳሪያዎች የሚውል 700 ሚሊዮን ዶላር ለመላክ እቅድ ያላቸው መሆኑን ባለፈው ሳምንት አስታውቀዋል፡፡ መሳሪያዎቹ ኢላማቸውን ብቻ ነጥለው መምታት የሚችሉ አራት የመካከለኛ ርቀት ሮኬቶችን፣ ሂሊኮፕተሮች፣ ጃቭሊን የተባለ ጸረ ታንክ መሳሪያ፣ ራዳሮች፣ የጦር ተሽከርካሪዎችና መለዋወጫዎችችን የሚያካትት መሆኑም ተመልክቷል፡፡
የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር “በቋሚነት እየተስፋፋ የሚገኘው የዩናይትድ ስቴትስ ማዕቀብ” ብለው ስለጠራው ማዕቀብ፣ ትናንት ሰኞ ባወጣው መግለጫ ፣ ሩሲያ በአጸፋው በ61 የዩናይትድ ስቴትስ ዜጎች ላይ የጣለችውን አዲስ ማዕቀብ ይፋ አድርጓል፡፡
በማዕቀቡ ውስጥ ከተካተቱት ውስጥ የዩናይትድ ስቴትስ ግምጃ ቤት ሹም ጃኔት ያለን እና የኔት ፍሌክስ ሥራ አስፈጻሚ ሪድ ሃስቲንግስ ይገኙበታል፡፡