የሩሲያ ጦርነት 100ኛ ቀኑን ባስቆጠረበት እለት ጦርነቱ በሁለቱ ቁልፍ የምስራቅ ዩክሬን ከተሞች ተፋፍሞ የቀጠለ ሲሆን፣ ሞስኮም ኪየቭም በጦር ሜዳ የበላይነት ማግኘታቸውን እየገለፁ ነው።
የክሬምሺን ቃል አቀባይ ዲሚትርይ ፔስኮቭ አርብ እለት እንደተናገሩት የሩስያ ወታደሮች፣ በምስራቅ ዩክሬን ተገንጣዮች በሚቆጣጠሩት ቦታ የሚገኙ ንፁሃን ዜጎችን የመጠበቅ ዋና ሀላፊነታቸውን በስኬት ተወጥተዋል ብለዋል።
አክለውም የሩሲያ ወታደሮች የተወሰኑ የዩክሬን አካባቢዎችን ነፃ ማውጣታቸውን እና ልዩ ወታደራዊ ዘመቻው ግቡን እስከሚመታ ድረስ ስራቸው እንደሚቀጥል ገልፀዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የሩሲያ ሀይሎች በሰቨርስኪ ዶኔትስ ወንዝ ላይ የሚገኘውን ድልድይ በፍንዳታ በማፈራረስ ዩክሬን ወደ ሴቬሮዶኔስክ ከተማ ወታደራዊ አቅርቦት እና ለንፁሃን ዜጎች ርዳታ እንዳታደርስ ማድረጋቸውን የሉናስክ ክልል አስተዳዳሪ ሰሪ ሀይዳይ ዛሬ አስታውቀዋል። ሀይዳይ ዛሬ በቴሌቭዥን በሰጡት መግለጫ በሴቬሮዶኔክስ የሚገኙ የዩክሬን ወታደሮች አሁንም እየተዋጉ መሆኑን እና የሩሲያ ሀይሎችን ከተለያዩ ቦታዎች ገፍተው እያስወጡ መሆኑን ገልፀዋል።