በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በትርፍ ስራ ምክንያት ክፍል የማይገቡ የዩንቨርስቲ መምህራን የትምህርት ጥራቱን እያጓደሉ ነው


በትርፍ ስራ ምክንያት ክፍል የማይገቡ የዩንቨርስቲ መምህራን የትምህርት ጥራቱን እያጓደሉ ነው
please wait

No media source currently available

0:00 0:07:43 0:00

በኢትዮጵያ የትምህርት ተደራሽነትን ለማስፋት በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የከፍተኛ ተቋማት ቁጥር ቢያድግም የትምህርት ጥራት ግን በከፍተኛ ደረጃ መውደቁን የተለያዩ የትምህርት ባለሙያዎች ይናገራሉ። ለትምህርት ጥራቱ መውደቅ ምክንያት ከሆኑት መሀል ደግሞ የሙሉ ግዜ አስተማሪዎች በተመደበው ግዜ በክፍል ያለመገኘት እና የአንድ ሴሚስተር ትምህርትን በአጭር ግዜ አስተምሮ ለመጨረስ መሞከር መሆናቸውን ያነጋገርናቸው ተማሪዎች እና መምህራን ነግረውናል።

በአምላክ መላኩ ከአመት በፊት ደብረብርሃን ዩንቨርስቲ ትምህርት ስትጀምር ያጋጠማት የመማር ማስተማር ሂደት ከጠበቀችው እጅግ የተለየ ነበር። መምህራን በተመደበላቸው የትምህርት ክፍለ ግዜ አይገኙም፣ አንዳንዶቹን ጭራሽ ሳያይዋቸው ሳምንታት ይቆጠራሉ።

በአምላክ እንደምትለው ለሳምንታት ክፍል ሳይገቡ የሚቀሩ አስተማሪዎች ያጓደሉትን ትምህርት የሚያካክሱት - አራት ወር የሚፈጀውን የአንድ ሴሚስተር ትምህርት በሁለት እና ሶስት ቀናት ውስጥ በማስተማር ነው።

በአምቦ ዩንቨርስቲ የሁለተኛ አመት የሲቪል ምህንድስና ተማሪ የሆነችው ቃልኪዳን ፀጋዬም - የመምህራን በተመደበው ሰዓት ክፍል አለመግባት የተለመደ ነው ትላለች።

ለመሆኑ መምህራን በትምህርት ገበታቸው ላይ የማይገኙት ለምንድ ነው? በአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩንቨርሲ መምህር የሆኑት አቶ ተሾመ ጎአ እንደሚሉት መምህራን የሚከፈላቸው ደሞዝ በቂ ባለመሆኑ ኑሮዋቸውን ለመደጎም በሚያደርጉት ሩጫ በትምህርት ገበታቸው ላይ እንዳይገኙ ያደርጋቸዋል። ለምሳሌ እሳቸው ከዋና ስራቸው ጎን ለጎን የጥናት እና የማህበራዊ አገልግሎት ስራዎችን ይሰራሉ።

አቶ ተሾመ በተጓዳኝ ስራ ምክንያት ክፍል ሳይገቡ ከቀሩ የቀሩበትን ግዜ ወዲያውኑ በማካካሻ ትምህርት እንዲሚያስተካክሉ ይናገርሉ። ሆኖም አንዳንድ 'ግዴለሽ' የሚሏቸው መምህራን የሙሉ ሴሚስተር ኮርስ በአንድና በሁለት ቀን ለመጨረስ መሞከራቸው የትምህርት ጥራቱ ላይ ጉዳት እያደረሰ መሆኑን ይገልፃሉ።

ይህ አይነቱ በጥድፊያ አስተምሮ ለመጨረስ የሚደረግ ጥረት ተማሪዎቹ ማግኘት የሚገባቸው በቂ እውቀት እንዳያገኙ ከማድረጉ በተጨማሪ ለከፍተኛ ጭንቀት እንደሚዳርጋቸውም ተማሪዎቹ ይገልፃሉ። በደብረ ብርሃን ዩንቨርስቲ ለምሳሌ ብዙ ተማሪዎች ፈተና ማለፍ እንዳልቻሉ በአምላክ ታስረዳለች።

ቃል ኪዳን እንደምትለው ደግሞ ፈተናውን ማለፍ ቢቻል እንኳን - በቂ ትምህርትና እውቀት ያላገኙ ተማሪዎች ለስራው ዓለም ብቁ አይሆኑም።

በአዲስ አስተዳደር መመራት ከጀምረ ስድስት ወራትን ያስቆጠረው የትምህርት ሚኒስቴር በቅርቡ ባካሄደው የዳሰሳ ጥናት የኢትዮጵያ የትምህርት ጥራት በከፍተኛ ሁኔታ እንዲወድቅ ካደረጉ ዋና ምክንያቶች ውስጥ የዩንቨርስቲ መምህራን በትምህርት ገበታቸው ላይ አለመገኘት መሆኑን አስታውቋል። በዚህ ዙሪያ ትምህርት ሚኒስቴርን በቀጥታ ለማናገር ያደረግነው ተከታታይ ጥረት ባይሳካም፣ በቅርቡ ከኢትዮጵያ ቴሌቭዥን ጋር ቆይታ አድርገው የነበሩት አዲሱ የትምህርት ሚኒስቴር ዶክተር ብርሃኑ ነጋ ይህን ብለዋል።

ለችግሩ መፍትሄ ለመፈለግ ከዩንቨርስቲዎችና መምህራን ጋር መነጋገር እና ለውጦችን መተግበር መጀመራቸው ለኢትዮጵያ ቴሌቭዥን የገለፁት ዶክተር ብርሃኑ የሁሉም ህብረተሰብ ክፍል አስተዋፅኦ እንደሚያስፈልግም አስምረውበታል።

ደብረ ብርሃን ዩንቨርስቲ ይሄ ለውጥ እየታየባቸው ካሉ ዩንቨርስቲዎች አንዱ ነው። የአንደኛ አመት ትምህርቷን እያጠናቀቀች ያለችው በእምነት እየተማረች ባለችው ሴሚስተር ከትምህርት ገበታው የቀረ አንድም መምህር የለም።

በአምቦ ዩንቨርስቲ ይህንን አይነቱን ለውጥ እንዳላየት የምትናገረው ቃልኪዳንም ተመሳሳይ ርምጃ ተወስዶ ተማሪዎች ለእውቀት እንጂ ለፈተና የማይማሩበትን ቀን ለማየት ትናፍቃለች።

XS
SM
MD
LG