በእስር ላይ የሚገኙ እና “ከሕግ አግባብ ውጪ መንግሥትን ከሥልጣን ለማስወገድ ተንቀሳቅሳችኋል” በሚል ተጠርጥረው ጉዳያቸው በፍርድ ቤት እየታየ የሚገኘው ሁለት የኦሮሞ ኒውስ ኔትዎርክ ኦኤንኤን ጋዜጠኞች እና 15 የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ኦነግ አመራሮች ለብይን ተቀጠሩ።
በኦሮምያ ክልል ጠቅላይ አቃቤ ሕግ ክስ ተመስርቶባቸው በክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ጉዳያቸው በመታየት ላይ የሚገኘው የ17 ተከሳሾች ዛሬ ፍርድ ቤት መቅረባቸውን ጠበቃቸው አቶ ሚልክያስ ቡልቻ ገልፀዋል። የኦኤንኤን ዘጋቢዎች ደሱ ዱላ እባ ቢቂላ አመኑ እንዲሁም በእነ ቃሲም አብዱላሂ የክስ መዝገብ ስር የሚጠሩ 15 የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ኦነግ አመራሮች፣ አባላትና ደጋፊዎች እንደሚገኙበት ጠበቃቸው ገልጸዋል።
ከዚህ ቀደም በነበረው ችሎት ክሱን እንዲያሻሽል ታዞ የነበረው ዐቃቤ ሕግ ክሱን አሻሽሎ ባለማቅረቡ ዛሬም ተመሳሳይ ትዕዛዝ መሰጠቱን ጠበቃው ገልፀዋል። ዐቃቤሕግ የዘዘውን ፈፅሞ ባለመገኘቱ እና የቀረበው ክስ የተሟላ ባለመሆኑ ፍርድ ቤቱ ተከሳሾችን በነጻ እንዲለቃቸው መጠየቻቸውን አቶ ሚልክያስ ገልጸዋል። ፍርድ ቤቱም ዐቃቤ ሕግ የሚሰጠውን ምላሽ ለማድመጥ ሰኔ 9 ቀን 2014 ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።
ተከሳሾቹ በአዲስ አበባ ከተማ ከረ ቆሬ በተባለ ስፍራ በጸጥታ ሀይሎች ተይዘው የታሰሩት ጥቅምት 8/2014 ዓ.ም መሆኑ ይታወሳል።