በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ሱዳን አስቸኳይ ጊዜ ዐዋጁን አነሳች እስረኞች ተለቀቁ


የሱዳን ወታደራዊ ባለሥልጣናት ባላፈው ጥቅምት የተካሄደውን መፈንቅለ መንግሥት ተከትሎ የታወጀው አስቸኳይ ጊዜ ዐዋጅ መነሳቱን ባስታወቁ ማግሥት በርካታ የፖለቲካ እስረኞችን መልቀቃቸው ተነግሯል፡፡

የማኅበራዊ አንቂ ቡድኖች የአስቸኳይ ጊዜ ጠበቆች ኮሚቴ ወታደራዊ መንግሥቱን በመቃወም ከተነሳው አመጽ ጋር በተያያዘ በፖርት ሱዳን የየታሰሩ 24 የማህበራዊ አንቂ ቡድን አባላት እንዲሁም ሌሎች 39 የሚሆኑት ከካርቱም አካባቢ መለቀቃቸውን አስታውቋል፡፡

የሱዳን ወታደራዊ መሪ ጀኔራል አብድል ፈታ አልቡርሃን ባላፈው እሁድ የአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጅ መነሳቱን ማስታወቃቸው በአገሪቱ መነጋገር እንዲኖር የሚያበረታታ መሆኑ ተነግሯል፡፡ ይሁን እንጂ ብዙ ሱዳናዊያን አክቲቪስቶች እምርጃው የተጨበጠ ለውጥ ስለማምጣቱና ወታደራዊው መንግሥት ሥልጣንን ወደ ሲቪል አስተዳደር ስለሚያሸጋግርበት ሁኔታ ጥርጣሬ አላቸው፡፡

ከዳርፉር የሰብአዊ መብት ተሟጋች የሆኑት መሀመድ ኡስማን “ይህ በፍጽም ምንም ለውጥ አያመጣም በፍጽሙ የጸጥታው ኃይል አሁንም ሙሉ ሥልጣን እንደያዘ ነው፡፡

ህጉን እንደፈለገው ነው የሚያደርገው ምንም ተጠያቂነት የለውም፡፡ ሰዎችን በዘፈቀደ እያሳደደ ማሰር የሚችል ነው ማንም የሚጠይቀው የለም ስለዚህ ይህ የአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጅ መነሳት ምንም ለውጥ አያመጣም፡፡” ይላሉ፡፡ ይህም ሆኖ በዳርፉር አሁንም አስቸኳይ ጊዜ አለመነሳቱን መሀመድ ሲገልጹ፣

“እንደ ሰብአዊ መብት ተሟጋችነቴ እኔ ከዳርፉር ነኝ ፣ ለ30 ዓመታት የቆዩ የአስቸኳይ ዐዋጅ አለ፡፡ አሁንም ድረስ ያለ፣ እስካሁን አልተነሳም፡፡” ብለዋል፡፡

የሰብአዊ መብት ተሟጋች የሆኑት መሀመድ ኡስማን ሳሌህ ይህንንም ቢሆን ወታደራዊ መንግሥቱ አስቸኳይ ጊዜውን በፈቃዱ ያነሳው አይመስልኝም ይልቁንም በሺዎች የሚቆጠሩ ሱዳናውያን የፖለቲካ ለውጥ እንዲመጣ በመጠየቅ፣ በየአደባባዩ የሚያሰሙት ተቃውሞ እየቀጠለ በመምጣቱ በተፈጠረ ግፊት ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡

XS
SM
MD
LG