በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ሦስት የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች በኢትዮጵያ እየተደረገ ነው ያሉት የጅምላ እስር እንዲቆም ጠየቁ


ሦስት የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች በኢትዮጵያ እየተደረገ ነው ያሉት የጅምላ እስር እንዲቆም ጠየቁ
please wait

No media source currently available

0:00 0:03:01 0:00

ሦስት የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች በኢትዮጵያ እየተደረገ ነው ያሉት የጅምላ እስር እንዲቆም ጠየቁ

የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ)፣ የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ፓርቲ (ኢህአፓ) እና እናት ፓርቲ በዛሬው ዕለት በጋራ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ የታሰሩ ጋዜጠኞች፣ የማኅበረሰብ አንቂዎችን እና ሌሎች በእስር ላይ የሚገኙ ሰዎች እንዲለቀቁ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ግለሰቦቹ የታሰሩት በሕግ ማስከበር ሰበብ መሆኑን ገልፀው፤ የሕግ ማስከበር ዘመቻው በሕጋዊ መንገድ ብቻ መከናወን እንዳለበትም አሳስበዋል፡፡

ፓርቲዎች ከዚህ ቀደም የኢትዮጵያ መንግሥት የሕግ የበላይነትን እና የዜጎችን በሰላም ወጥቶ የመግባት መብት እንዲያረጋግጥ ሲወተውቱ መቆየታቸውን አስታውሰው፣

“የሕግ ይከበር ጩኸቶች ሰሚ አጥተው ሀገር የጥቂት ቡድኖች ሀብት ወደ መምሰል እየተጓዘች ነው” ብለዋል፡፡

ሀገሪቱ በዚህ ሁኔታ ውስጥ እያለችም መንግሥት በአማራ ክልል ሕግ ማስከበር በሚል የጀመረውን ዘመቻ ተቃዋሚ ፓርቲዎችን፣ ምሑራንን፣ ጋዜጠኞችንና የማኅበረሰብ አንቂዎችን ለማሳደድ እየተጠቀመበት መሆኑን በመግለጫቸው ላይ አስፍረዋል፡፡ መንግሥት በዚህ ሂደት ያሰራቸውን ሰዎች እንዲለቃቸውም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በዚህ የፓርቲዎች መግለጫ ላይ ከመንግሥት የተሰጠም ምላሽ የለም። የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ዓርብ መጋቢት 12 ባወጣው መግለጫ፣ በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የሚታየውን ሕገወጥነት እና የሰላም መደፍረስ እንዲሁም ሥርዓት አልበኝነትን መንግሥት እንዲቆጣጠር መላ ሕዝባችን በተደጋጋሚ ሲጠይቅ ቆይቷል ያለ ሲሆን፣ ከሰሞኑ አዲስ አበባን ጨምሮ በሁሉም ክልሎች ውስጥ የፌዴራልና የክልል የፀጥታ ኃይሎች እየወሰዱት ነው ያለው ሕግ የማስከበር እርምጃ ብሔራዊ የፀጥታ ም/ቤት በወሰነው መሰረት እንደሆነ ጠቁሟል፡፡

አክሎም “ነፃነትንና መብትን ከለላ በማድረግ የሚፈፀም የትኛውም ዓይነት እኩይ ተግባርን መንግስት አይታገስም” ብሏል፡፡

የሚዲያ ባለሞያዎችን የእስር ሁኔታ በመከታተል ላይ መሆኑን የገለጸው የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ባለፈው ዓርብ ባወጣው መግለጫ፣ የሚዲያ ባለሞያዎች መታሰራቸው በተለይ የሚዲያ ሕጉን የሚጻረር መሆኑን በመጥቀስ የታሰሩት እንዲለቀቁ ጠይቋል፡፡

ዘገባው የገብረሚካኤል ገብረመድኅን ነው።

XS
SM
MD
LG