የአፍሪካ መሪዎች በአህጉሪቱ እያደገ ስለመጣው ሰብአዊ እርዳታ፣ እየተስፋፋ ስላለው የአክራሪነት ጥቃት፣ የአየር ንብረት ለውጥ ፈተናዎችና ስለ ወታደራዊ መፈንቅለ መንግስቶች ለመምከር፣ በኢካቶሪያል ጊኒ ማላቦ ውስጥ ተሰብስበዋል፡፡
ትናንት በተጀመረውና ዛሬም በቀጠለው ስብሰባ መሪዎቹ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ተፈናቃዮችንና በምግብ እጥረት የተጠቁ ወደ 280 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎችን የጎዳውን ሰብአዊ ቀውስ ለመፍታት አስቸኳይ እምርጃዎች መወሰድ እንደሚኖርባቸው ጥሪ አድርገዋል፡፡
የደህንነት አለመኖርና አለመረጋጋት ሁኔታዎች እየበዙ መምጣታቸው፣ በተለይም ከሰሃራ በታች ባለው በረሃ፣ ካለፈው የካቲት ወዲህ የጂሃድሲቶች መስፋፋት፣ እንዲሁም ከአል ቃይዳ እና እስላማዊ መንግስት ቡድኖች ጋር የተገናኙ ቡድኖች በሺዎች የሚቆጠሩ ስደተኞችን መግደላቸው፣ ወደ ሁለት ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች እንዲፈናቀሉ ማድረጋቸው ተመልክቷል ሲል አሶሼይትድ ፕሬስ ዘግቧል፡፡
ከዚህ በፊት ታይተው የማይታወቀው ድርቅ ከፍተኛ የረሀብ አደጋ የደቀነባቸው በርካታ አካባቢዎች መኖራቸውም ተጠቅሷል፡፡
አፍሪካ ኒውስ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽነር ሙሳ ፋቂ መግለጫን ጠቅሶ እንደዘገበው በዚህ ዓመት 113 ሚሊዮን አፍሪካውያን አጣዳፊ የሰብአዊ እርዳታ የሚፈልጉ ናቸው፡፡
ስብስባው ላይ ወደ 20 የሚጠጉ የአፍሪካ መሪዎች መካፈላቸውም ተዘግቧል፡፡