የዩክሬኑ ፕሬዚዳንት ቮሎድሚር ዘለነስኪ በሚያስተላልፉት ዕለታዊ መልዕክታቸው ሩሲያ በዩክሬናውያን ላይ “የዘር ማጥፋት ፖሊሲዋን በግልጽ እያካሄደች ነው” ሲሉ በዛሬው እለት ተናገሩ፡፡
“ዓለም ሩሲያን ጥንካሬ ባይሰጣት ኖሮ ጦርነቱን ማቆም ይቻል ነበር” ያሉት ዘለንስኪ “ሩሲያ ለአውሮፓ ከምታቀርበው ነዳጅ በየቀኑ በቢሊዮን የሚቆጠር ዩሮ እያገኘች ነው” ብለዋል፡፡ የአውሮፓ ህብረት አባላት ሩሲያ ላይ እንዲጣል ስድስት ጉዳዮችን ባካተተው ማዕቀብ ከስምምነት ለመድረስ እየሞከሩ ነው፡፡ “ዩክሬን ነጻ አገር ስለሆነች ጨርሶ አትሰበርም” ያሉት ዘለንስኪ፣ ይልቁንም አሁን ያልተመለሰው ጥያቄ “ትርጉም አልባ በሆነው በዚህ ጦርነት፣ ህዝባችን ለነጻነቱ የሚከፍለው መስዋዕትነት ምን ይሆናል የሚለው ነው፡፡” ሲሉ ጠይቀዋል፡፡
በሰሜን ምስራቅ ዩክሬን ወደ ሩሲያ ድንበር አቅጣጫ የተገፉት የሩሲያ ኃይሎች መልሰው ለማጥቃት በዝግጅት ላይ በመሆናቸው 3 ወር የዘለቀው ጦርነት በቅርብ የሚበቃበት ሁኔታ ግልጽ አለመሆኑን ምዕራባውያን ባላሥልጣናት ይናገራሉ፡፡ ከባድ ውጊያ በሰሜንና ምስራቅ ከተሞች እየተካሄደ ሲሆን፣ የዩክሬን ሁለተኛዋ ትልቅ ከተማ በሆነቸው ካርኪቭ የሚገኙ ባለሥልጣናት ትናንት ሀሙስ ሩሲያ ባደረሰችው ድብደባ ቢያንስ ሰባት ሰላማዊ ሰዎች መገደላቸውና 17 ሰዎች መቁሰላቸው ገልጸዋል፡፡
በካርኪቭ ያሉ የዓይን እማኞች የሩሲያ ኃይሎች በከተማው በስተሰሜን ያላቸውን ይዞታ ለማጠናከር በተከታታይ በሚያደርጉት ተኩስ ፍንዳታዎች ይሰሙ እንደነበር ተናግረዋል፡፡ ምንም እንኳ የሩሲያ ኃይሎችን ወደ ሁላ መግፋት የተቻለ ቢሆንም ሩሲያውያኑ መልሰው ለማጥቃት ከፍተኛ ሙከራ እያደረጉ መሆኑን ባለሥልጣናቱ ገልጸዋል፡፡
የካርኪቭ አገረ ገዥ ኦሌ ሲነሁቦቭ “ዘና ለማለት ጊዜው ገና ነው፣ ጠላት አሁንም ባልተጠበቀ ሁኔታ ሰላማዊ ሰዎችን እየደበደበና እያሸበረ ነው” ብለዋል፡፡ ምንም እንኳ የሩሲያ ጦር በማህበራዊ ድረገጾቹ የዶናባስን ግዛት ጨምሮ፣ በዩክሬናውያን ኃይሎች ላይ ድልን እየተቀዳጀ መሆኑን ቢገልጽም፣ የሩሲያ ባለሥልጣናት በካርኪቭ ስላለው ሁኔታ እስካሁን የተናገሩት ነገር የለም፡፡
አንድ ከፍተኛ የዩናይትድ ስቴትስ ባለሥልጣን፣ በካርኪቭ ውጊያው እየጨመረ ስለመሆኑ ከሚቀርበው ሪፖርት ውጭ አዲስ ነገር አለመኖሩን ትናንት ሀሙስ ተናግረዋል፡፡ ስማቸውን እንዳይገለጽ የፈለጉት ባለሥልጣን ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት “እስካሁን እንደምናየው የዩክሬን ኃይሎች የሩሲያን ሃይሎች ከከተማው አርቀው እየገፏቸው ነው፡፡ በሩሲያ ድንበር ውስጥ ከጥቂት እስከ 10 ኪሎሜትር በላይ ርቀት ያለው አካባቢ ቢሆን ነው” ብለዋል፡፡
ባለሥልጣኑ ጨምረው እንደገለጹት “በስተምስራቅ በኩል የሩሲያ ኃይሎች እንደ ፖፓሳና እና ሲቪየሮዳነትስክ የመሳሰሉ ከተሞችን በመቆጣጠር ቀስ በቀስ መጠነኛ ውጤት እያገኙ ቢሆንም አብዛኞቹ የምስራቅ ከተሞች በዩክሬን ኃይሎች ቁጥጥር ስር ናቸው” በማለት ያለውን ሁኔታ ገልጸዋል፡፡