በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በጦርነት የተፈናቀሉ ኢትዮጵያውያን ወደ መኖሪያቸው ለመመለስ የሚያስችል ሁኔታ እንደሌለ ተናገሩ


በጦርነት የተፈናቀሉ ኢትዮጵያውያን ወደ መኖሪያቸው ለመመለስ የሚያስችል ሁኔታ እንደሌለ ተናገሩ
please wait

No media source currently available

0:00 0:05:11 0:00

በጦርነት የተፈናቀሉ ኢትዮጵያውያን ወደ መኖሪያቸው ለመመለስ የሚያስችል ሁኔታ እንደሌለ ተናገሩ

በአብዛኛው የኢትዮጵያ አፋር ክልል አካባቢ ሲካሄድ የቆየው ግጭት ቢቆምም፣ የትግራይ ሀይሎች ክልሉንከተቆጣጠሩ በኃላ ቤታቸውን ጥለው ለመሰደድ የተገደዱ የአፋር ተወላጆች ግን ወደ መኖሪያቸው መመለስ አልቻሉም።በዚህ ጦርነት የተጎዱት የትግራይ ተወላጆች ብቻ ሳይሆኑ በአፋር ክልልም የተካሄደው ጥቃት መኖሪያ ቤቶቻቸውን እናመተዳደሪያቸውን ሙሉ ለሙሉ እንዳወደመው ለስደት የተዳረጉ ሰዎች ይናገራሉ።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት፣ በትግራይ ክልል ከሚካሄደው ግጭት ጋር ተያይዞ ወደ 700 ሺህ የሚጠጉ ሰዎች ከቤት ንብረታቸው እንደተፈናቀሉ ባስታወቀበት የኢትዮጵያ አፍር ክልል ከሚገኙ መጠለያ ጣቢያዎች - ይህ አንዱ ነው።

ከተፈናቃዮቹ የተወሰኑትም በዚህ ከክልሉ ዋና ከተማ ሰመራ በ100 ኪሎሜትር ርቀት ላይ በሚገኘው መጠለያ ውስጥ ተጠልለው ይገኛሉ።

የአፋር ክልል ከትግራይ ክልል ጋር ረጅም ግዜ የቆየ ቁርኝት ያለው በመሆኑ የህወሃት ሀይሎች ጥቃት ሲያደርሱባቸው፣ ለነዋሪዎቹ ያልጠበቁት ድርጊት ሆኖባቸዋል። ከተፈናቃዮቹ አንዷ ሀሊማ ጣሂር እስማኤል ስለሁኔታው እንዲህ ታስረዳለች።

"ተኝተን ነበር። የከባድ መሳሪያ ተኩስ ሰማን። ስንነሳ የጦርነት ቀጠና ውስጥ ነበርን። ባሎቻችን እና ልጆቻችን ተበታተኑ። በመኖሪያችን ላይ በተከፈተው ከፍተኛ ተኩስ ምክንያት ቤታችንን ጥለን ተሰደድን።"

ሀሊማ ከአምስት አመት በታች ከሆኑ ሶስት ልጆቿ ጋር ሆና ነው የተሰደደችው። ከጥቂት ልብሶች በስተቀር ምንም ነገር አልያዙም። አሁን ልክ እንደሌሎቹ ተፈናቃዮች የእርዳታ እጅ እየጠበቁ ይኖራሉ።

የትግራይ ሀይሎች ጥቃት ባደረሱባቸው የአፋር ክልል አካባቢዎች የቆዩ አንዳንድ ሰዎች እንደነገሯትም፣ መተዳደሪያዋ የነበረው የሸቀጣ ሸቀጥ ሱቅ ተዘርፎ ሙሉ ለሙሉ ወድሟል። ኮናባ በሚባለው አካባቢ የሚገኘው የቤተሰቦቿ መኖሪያ ቤትም እንዲሁ ወድሟል።

"አሁን እንዴት አርገን ወደ ኮናባ እንመለሳለን? ወደ ኮናባ ብንመለስ ውሃ የለም፣ ንብረታችን፣ መገልገያ የቤት እቃዎቻችን በሙሉ ተዘርፏል።"

ሀኢማ እንደምትለው ከጦርነቱ በፊት እንደሷ የተሻለ ኑሮ ይኖር የነበረውም ሆነ ድሃው የህብረተሰብ ክፍል፣ አሁን ሁሉም እኩል ደህይቷል።

ቫለሪ ብራውኒንግ፣ ላለፉት ሰላሳ አመታት በክልሉ በጎ ፈቃደኛ ሆና ስታገለግል የኖረች ነርስ ናት። በሚያዚያ ወር ተዋጊ አካላት የሰብዓዊ ርዳታ እንዲደርስ በማለት ያደረጉትን ስምምነት ተከትሎ ጦራቸውን ካስወጡ በኃላ፣ በሰሜናዊው የአፋር አካባቢ የሚኖሩ ማህበርሰቦችን ጎብኝታ ነበር።

"ሆን ተብሎ የተፈፀመ ውድመት ነው። ቤት ለቤት እየሄዱ ነው ዝርፊያ የፈፀሙት። በየሰዉ ቤት እየሄዱ ሁሉንም ዘርፈዋል። ተቋማትን፣ የመንግስት ተቋማትን ደግሞ ወይ አቃጥለዋቸዋል፣ በቦምብ መተዋቸዋል ወይም መሳሪያዎችን ሁሉ ነቃቅለው አበለሻሽተው ገነጣጥለዋቸዋል።"

የዓለም ምግብ ፕሮግራም እና ሌሎች የሰብዓዊ ርዳታ ሰጪ ቡድኖች ምግብ እና ሌሎች የእርዳታ ቁሳቁሶችን እያከፋፈሉ ቢሆንም በተለይ ርቀት ባላቸው አካባቢዎች እና ለመንገድ አመቺ ባልሆኑ ስፍራዎች የሚገኙ ሰዎችን መድረስ አስቸጋሪ ነው።

በአሁኑ ወቅት ከክልሉ ህዝብ ከግማሽ በላይ የሚሆነው 1.3 ሚሊየን ህዝብ ርዳታ የሚያስፈልገው ቢሆንም የዓለም ምግብ ፕሮግራም እስካሁን መድረስ የቻለው ለ630 ሺህ ሰዎች ነው። ከዚህ ተጨማሪ ሌላ የረጅም ግዜ ስጋት እንዳለም የፕሮግራሙ ተወካይ ክሪስቲን ሀኮንዜ ያስረዳሉ።

"ከዚህ በኃላ ስለሚሆነውም ማሰብ አለብን። ሰዎች ወደአካባቢያቸው ሲመለሱ ልጆቻቸውን ምንድነው የሚመግቡት? ስለዚህ ርዳታ ሰጪዎች በተለይ የገንዘብ ድጋፍ በማድረግ እንዲረዱን እንፈልጋለን። እኛ ለእያንዳንዱ ቤተሰብ መተዳደሪያቸውን እንዲያገኙ እንደግፋቸዋለን።"

የአፋር ክልላዊ መንግስት ባካሄደው ቅድመ ዳሰሳ በክልልሉ 20 ቢሊየን የኢትዮጵያ ብር ወይም 388 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር የሚያወጣ ውድመት መድረሱን አስታውቋል።

በአካባቢው ውሃ የለም፣ በብዙ ቦታዎች የጤና ተቋማት እና ትምህርት ቤቶች አገልግሎት አይሰጡም። መሀመድ ሀሰን በአፋር ክልል የአደጋ መከላከል እና ምግብ ዋስትና ቢሮ ሀላፊ ናቸው።

"ማህበረሰቡን ወደመጣበት ለመመለስ መሰረተ ልማቶች እንደገና መዘርጋት ይኖርባቸዋል። ሁሉንም ነገር ወደ ነበረበት ለመመለስ እና መልሶ ግንባታ ለማካሄድ ያለን አቅም እጅግ ውሱን ነው። ስለዚህ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ትኩረት እንዲሰጠንና የሚያስፍልገንን ግብዓት በማሰባሰብ እንዲያግዘን ጥሪ አቀርባለሁ። "

የዓለም ባንክ ሀገሪቱን በድጋሚ ለመገንባት የገንዘብ ድጋፍ አድርጓል። ሆኖም አቶ መሀመድ እንደሚሉት እንደ እስማኤል ያሉት ተፈናቃዮች ወደ ቤታቸው በሰላም እንዲመለሱ የበለጠ ርዳታ ማግኘት ያስፈልጋቸዋል።

XS
SM
MD
LG