የኮቪድ-19 ወረርሽኝ “በጣም በርግጠኝነት አላበቃም” ሲሉ የዓለም ጤና ድርጅት ዳይሬክተር ቴድሮስ አድሃኖም ገ/ኢየሱስ ትናንት ዕሁድ በተካሄደው የ75ኛው የዓለም ጤና ጉባኤ ላይ ተናገሩ፡፡
የዳይሬክተሩ ማስጠንቀቂያ የመጣው በርካታ አገሮች እያገረሸ ባለው የኮቪድ-19 ወረረሽኝ ሳቢያ ቀደም ሲል ያወጧቸውን አስገዳጅ መመሪያዎች ወደ ቦታቸው እየመለሱ ባሉበት ወቅት ነው፡፡
“በሁሉም የዓለም ክፍሎች በሚገኙ 70 አገሮች ውስጥ የተጋላጮች ቁጥር መጨመራቸውን ዘገባዎች ያመለክታሉ” ያሉት ዶ/ር ቴድሮስ
“ይህ ቫይረስ ሁሌም አመጣጡ ያስገርመናል፣ ማኅበረሰቡን እየደጋገመ አሁንም አሁንም በማዕበሉ ይመታል፣ እስካሁን አቅጣጫውንም ሆነ መጠኑን ጨርሶ መገመት አልቻልንም” ብለዋል፡፡
የዓለም ጤና ድሬክተሩ በመላው ዓለም በኮሮናቫይረስ የሞቱት ሰዎች ቁጥር ከ6ሚሊዮን ይበልጣል ያሉ ሲሆን፣ የተባበሩት መንግሥታት ግን ከዚህ የሚበልጥ መሆኑን ገልጾ ወደ 15 ሚሊዮን የተጠጉ ሰዎች መሞታቸውን አመልክቷል፡፡