የዩናይትድ ስቲትስ ፕሬዚደንት ጆ ባይደን በእስያ ጉብኝታቸው ቴክኖሎጂ ዘርፍ ላይ አተኩረዋል
የእስያ ጉብኝታቸውን በዩናይትድ ስቴትስ የቴክኖሎጂ ዘርፍ ላይ በማትኮር የጀመሩት የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚደንት ጆ ባይደን በደቡብ ኮሪያ የሳምሰንግ ኩባኒያን የኮምፒዩተር ቺፕ ማምረቻ ጎብኝተዋል፡፡ ባይደን የጎበኙት ስፍራ የደቡብ ኮሪያው የኤሌክትሮኒክ ኩባኒያ ሳምሰንግ ዩናይትድ ስቴትስ ቴክሳስ ውስጥ ከኦስተን ከተማ ወጣ ብሎ በአስራ ሰባት ቢሊዮን ዶላር ወጪ ለሚገነባው የኮምፒዩተር ቺፕ ማምረቻ ፋብሪካ በሞዴልነት የሚያገለግል መሆኑ ተጠቁሟል፡፡
ፕሬዚደንት ባይደን በደቡብ ኮሪያ እና በጃፓን በሚያካሂዱት የስድስት ቀናት ጉብኝት የሚያስተናግዷቸው በርከት ያሉ የውጭ ፖሊሲ ጉዳዮች ያሉ ቢሆንም ጉብኝታቸውን ለሀገራቸው ህዝብ አሳሳቢ በሆኑ ጉዳዮች ላይ እንዲያተኩር አድርገው አዘጋጅተውታል፡፡
የዋይት ሀውስ የብሄራዊ ጸጥታ አማካሪ ጄክ ሰለቫን በሰጡት ቃል ሳምሰንግ ቴክሳስ ውስጥ በሚያፈስሰው መዋዐለ ነዋይ ለአሜሪካውያን ጥሩ ደመወዝ የሚከፈልበት የስራ እድል የሚፈጥር ሲሆን የምርቱን የአቅርቦት ሰንሰለት ለማጠናከር የሚጠቅም እንደሆነ አስረድተዋል፡፡