በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ሰሜን ኮሪያ  ትኩሳት ያላቸው ዜጎቿ ቁጥር ከ2 ሚሊዮን ቢያልፍም ኮቪድን በመዋጋት ጥሩ ርምጃ አስመዝግቤአለሁ አለች


እ.አ.አ በ ግንቦት 18 2022 ዓ.ም የሰሜን ኮሪያ ማዕከላዊ የዜና ማሰራጫ የለቀቀው ምስል የባቡር ጣቢያ ሰራተኞች ኮቪድ 19ን ለመከላከል የፒዮንግያንግን ጣቢያ አካባቢ መድሃኒት ሲረጩ ያሳያል
እ.አ.አ በ ግንቦት 18 2022 ዓ.ም የሰሜን ኮሪያ ማዕከላዊ የዜና ማሰራጫ የለቀቀው ምስል የባቡር ጣቢያ ሰራተኞች ኮቪድ 19ን ለመከላከል የፒዮንግያንግን ጣቢያ አካባቢ መድሃኒት ሲረጩ ያሳያል

ኮቪድ አስራ ዘጠኝ ወረርሽኝ በሀገሩዋ መኖሩን ለመጀመሪያ ጊዜ ያመነችው ሰሜን ኮሪያ የትኩሳት ህመም የሚሰማቸው ዜጎችዋ ቁጥር ከ2 ሚሊዮን ቢያልፍም ወረርሽኙን በማዋጋት ረገድ ጥሩ ርምጃ አስመዝግቤአለሁ አለች፡፡

ሰሜን ኮሪያ ወረርሺኙ እየተዛመተ መሆኑን ባለፈው ሳምንት ለመጀመሪያ ጊዜ ማረጋገጧን ተከትሎ በኒውክሊየር መሳሪያ መርሃ ግብሯ ምክንያት ከባድ ማእቀብ የተጣለባት ሀገር የህክምና አቅርቦት እና የክትባት እጥረት ጉዳይ ስጋት ፈጥሯል፡፡

ሰሚን ኮሪያ የቆዩ ባላንጣዎቹዋ የሆኑት ጎረቤቷ ደቡብ ኮሪያ እና ዩናይትድ ስቴትስ እርዳታ ለመላክ ፍላጎታቸውን ቢገልጹም መልስ አለመስጠቷን የደቡብ ኮሪያ ባለስልጣናት ገልጸዋል፡፡

የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚደንት ጆ ባይደን ዛሬ ደቡብ ኮሪያ የገቡ ሲሆን ከአዲሱ ፕሬዚደንት ዩን ሱክ ዬዎል ጋር ሰሜን ኮሪያን ለመርዳት ስለሚቻልበት መንገድ ይነጋገራሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ሰሜን ኮሪያ ትኩሳት የያዛቸው ተጨማሪ 263 ሺህ 370 ሰዎች መገኘታቸው አና ሁለት ሰዎች መሞታቸውን የገለጸች ሲሆን አጠቃላዩ ቁጥር ከሁለት ሚሊዮን ማለፉን እና ከዚህ ውስጥ ስድሳ አምስት ሰዎች መሞታቸውን የሀገሪቱ መንግሥት የዜና ማሰራጫዎች ዘግበዋል፡፡

ሀገሪቱ የኮቪድ መመርመሪያ እጥረት ያለባት ሲሆን ትኩሳት ህመም ከሚሰማቸው ዜጎቹዋ ውስጥ ምን ያህሉ ለኮሮና ቫይረስ የተጋለጡ እንደሆኑ አላሳወቀችም፡፡

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ወረርሺኙ በሃያ አምስት ሚሊዮኑ የሀገሪቱ ህዝብ ላይ ከባድ ጉዳት የሚያስከትል መሆኑን ገልጾ ያስጠነቀቀ ሲሆን የዐለም የጤና ድርጅት በበኩሉ ወረርሺኙ በቁጥጥር ስር ካልዋለ ይበልጡን ገዳይ የሆኑ የቫይረሱን ዝርያዎች እንዲከሰቱ ሊያደርግ ይችላል የሚል ስጋት እንዳለው አስታውቋል፡፡

XS
SM
MD
LG