በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የአዲሱ የሶማሊያ ፕሬዝዳንት የመቶ ቀናት ውጥኖች እና ተስፋ


አዲሱ የሶማሊያ ተመራጭ ፕሬዝዳንት ሃሰን ሼክ ሞሃሙድ
አዲሱ የሶማሊያ ተመራጭ ፕሬዝዳንት ሃሰን ሼክ ሞሃሙድ

“አዲሱ የሶማሊያ ተመራጭ ፕሬዝዳንት ሃሰን ሼክ ሞሃሙድ በመጀመሪያዎቹ መቶ የሥራ ቀናት መንግስታቸው በፀጥታ፣ የሃገሪቱን ምጣኔ ሃብት ለማንሰራራት በታለሙ ሥራዎች፣ የፖለቲካ መረጋጋት እና የዕዳ ስረዛ ላይ አስቸኳይ ትኩረት ያደርጋል” ሲሉ አስታወቁ።

እንደ አውሮፓውያን የዘመን አቆጣጠር ከ2012 እስከ 2017ዓም በፕሬዝዳንትነት ያገለገሉት ሞሃሙድ ባለፈው እሁድ በተካሄደው ምርጫ ነው፤ ተሰናባቹን ፕሬዝዳንት ሞሃመድ አብዱላሂ መሃመድን አሸንፈው ለሁለተኛ ጊዜ ለስልጣን የበቁት።

"በመጀመሪያዎቹ አንድ መቶ የሥራ ቀናቴ ማሳካት የምንፈልገውን ተግባራዊ ማድረግ እንሻለን። የቀድሞውን የሕግ ስርዓት አደረጃጀት እና የደህንነት ተቋማቶቻችንን መዋቅር ማሻሻል እንፈልጋለን፤ እንዲሁም የጸጥታ መዋቅሩን ፌደራላዊ ማድረግ እንፈልጋለን፤” ሲሉ ሃሰን ሼክ ሞሃሙድ በተለይ ከአሜሪካ ድምጽ የሶማልኛ ክፍል ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ተናግረዋል።

ከቅርብ ወራት ወዲህ በሞቃዲሾ ጥቃቱን ካጠናከረው አሸባሪ ቡድን ከአልሸባብ ጋር የሚያደርጉት ትግል አዲሱን ፕሬዝዳንት ከሚጠብቁት ፈተናዎች ትልቁ ነው። ከተቋቋመበት ከዛሬ 15 ዓመት በፊት አንስቶ ከአልቃይዳ ጋር ቁርኝት ያለውን አልሸባብን ድል መንሳት ከሞሃሙድም ሆነ ከተቀሩት የሶማሊያ ፕሬዝደንቶች አቅም በላይ ሆኖ ነው የቆየው። በመጀመሪያ የስልጣን ዘመናቸው ወቅት ከተቃጡባቸው ተደጋጋሚ የግድያ ሙከራዎች የተረፉት ሞሃሙድ አልሸባብ የሚደቀነውን ፈተና በቅርብ ይረዳሉ።

ይሁን እንጂ “ሶማሊያ ወደፊት ትገሰግሳለች” ሲሉ በሙሉ ልብ ለሚናገሩት ሞሃሙድ ዋና ከተማይቱን ሞቃዲሾን ከጥቃት ማስጠበቅ በመጀመሪያዎቹ 100 ቀናት የስልጣን ጊዜያቸው ቅድሚያ ከሚሰጧቸው ክንዋኔዎች መካከል አንዱ መሆኑን አመልክተዋል።

አዲሱ ፕሬዝዳንት አክለውም "የሞቃዲሾን ደህንነት ለማስጠበቅ ከታችኛውና ከመካከለኛው ሸበሌ ግዛቶች የሚነሱትን እና ወደ ከተማይቱ የሚያመሩትን የመተላለፊያ መንገዶች ጥበቃ ማረጋገጥ፤ እንዲሁም በከተማይቱ ውስጥ ጠንካራ የመረጃ መረብ መዘርጋት ያስፈልጋል። ደህንነትን ለማረጋገጥ በምናደርገው ጥረት ሊረዳን ከሚፈልግ ማንኛውም ወገን ድጋፍ እና ትብብር እንጠይቃለን።" ነው ያሉት።

ተመራጩ ፕሬዝዳንት በተለይ ከአሜሪካ ድምጽ ጋር ካደረጉት ልዩ ቃለ ምልልሳቸው ሰዓታት አስቀድሞ የዩናይትድ ስቴትስ ልዩ ወታደራዊ ኃይል አባላት አሸባሪውን ቡድን ለመዋጋት የሚደረገውን ዘመቻ ለመደገፍ ወደ ሶማሊያ እንደሚመለስ ይፋ የተደረገበትን ዜና በይሁንታ ነው የተቀበሉት።

ከትላንት በስቲያ ማክሰኞ በትዊተር ገፃቸው ላይ ባሰፈሩት ጽሁፍ ለውሳኔው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደንን አመስግነው “መረጋጋት በመሻት እና ሽብርተኝነትን ለመዋጋት በምናደርገው ጥረት የሚተማመኑበት አጋር” ሲሉ ዩናይትድ ስቴትስን አወድሰዋል።

የእሁድ ዳግም የመመረጣቸው ዜና የመጣው በፕሬዝዳንቱ እና በጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዲሁም በፌደራሉ መንግስት እና በግዛቶች መካከል አንድ ዓመት ለተቃረበ ጊዜ የዘለቀ ያለመግባባት እና የፖለቲካ አለመረጋጋት ተከትሎ ነው።

ብጥብጡ የተቀሰቀሰው እና ለመፈንዳትም ተቃርቦ የነበረው እንደ አውሮፓውያን የዘመን አቆጣጠር በየካቲት ከ2021ዓም የሃገሪቱ ፓርላማ የፕሬዚዳንት ሞሃመድ አብዱላሂን የስልጣን ዘመን ለሁለት ዓመት ለማራዘም የውሳኔ ሃሳብ ባቀረበበት ወቅት ነው። ሆኖም የሸንጎ አባላቱ ከአገር ውስጥ እና ከውጭ አገር የደሰረባቸውን ከፍተኛ ጫና ተከትሎ የቀደመ ውሳኔያቸውን ሊቀይሩ ተገደዋል።

የስልጣን ዘመናቸውን ሲጀምሩ ብርቱ ሥራዎች የሚጠብቋቸው ሃሰን ሼክ ሞሃሙድ ሃገሪቱን ወደ ሰላም እና ወደ እርቅ ለማምራትም ቃል ገብተዋል።

"የፖለቲካ መረጋጋት መፍጠር ሌላው በመጀመሪያዎቹ 100 የሥራ ቀናቴ ለማሳካት ቅድሚያ ከምሰጣቸው ጉዳዮች አንዱ ነው።” ያሉት ሃሰን ሼክ ሞሃሙድ በተጨማሪም “የፌዴራል አስተዳደሩ አባል ከሆኑ ግዛቶች መሪዎች ጋር ጸጥታን ጨምሮ በጣም አስፈላጊ የሆኑ ጉዳዮችን ፌዴራላዊ የሚያደርግ ሁሉን አቀፍ ስምምነት መፍጠር አለብን” ብለዋል።

በስልጣን ዘመናቸው “ጎሳን መሰረት ያደረገውን ውስብስብ የምርጫ ቀመር በመፋቅ ሶማሊያን አንድ ሰው-አንድ ድምጽ ወደሚለው ሥርዓት ለማምራት እቅድ አውጥተው የሚሰሩ መሆናቸውንም ተናግረዋል።

“በ2016ቱን ፕሬዚዳንታዊ ሥልጣኔን ባስረከብኩበት ወቅት ሃገሪቱን ወደተለየ የድምፅ አሰጣጥ ስርዓት ሊወስድ የሚችል ዝርዝር እቅድም አስረክቤ ነበር። አሁን እቅዴ ሶማሊያ ወደ አወዛጋቢው ጎሳን መሰረት ያደረገ የሥልጣን ክፍፍል አሰራር እንዳትመለስ ለማድረግ መስራት ነው።” ሲሉ ዕቅዳቸውን ለአሜሪካ ድምጽ አስረድተዋል።

ተመራጩ ፕሬዝዳንት በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትርን እንደሚሰይሙና በሶማሊያ ፕሬዝዳንቶች እና ጠቅላይ ሚኒስትሮች መካከል ያለውን ስር የሰደደ የስልጣን ሽኩቻ ለመፍታት የተነደፉትን የህግ ማሻሻያዎችን በማዘጋጀት ያለፉትን መንግስታት ጥረት ያደናቀፈ እና በፌዴራል መንግስት ተቋማት መካከል ያለው ትብብር እንዲዳከም ያደረገ አሰራር ለመተካት እንደሚሰሩ ተናግረዋል።

XS
SM
MD
LG