በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ዚምባቡዌ ከህገ ወጥ አዳኞች ላይ የወረስኩት የዝሆን ጥርስ ክምችቴን እንድሸጥ ይፈቀድልኝ ስትል ጠየቀች


የአውሮጳ ሀገራት አምባሳደሮች የዝሆን ጥርስ ክምችትን ሲጎበኝ ሃራሬ እአአ ግንቦት 16/2022
የአውሮጳ ሀገራት አምባሳደሮች የዝሆን ጥርስ ክምችትን ሲጎበኝ ሃራሬ እአአ ግንቦት 16/2022

ሀገሪቱ ውስጥ ያሉት ዝሆኖች ቁጥር በአደገኛ ሁኔታ በፍጥነት እየጨመረ ነው ያለችው ዚምባቡዌ ለጥበቃቸው በአስቸኳይ የሚያስፈልጋትን ስድስት ሚሊዮን ዶላር በእጄ ያለውን የዝሆን ጥርስ ሸጬ እንዳገኝ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ይተባበረኝ ስትል ዚምባቡዌ ጠይቃለች።

የዚምባቡዌ የዱር አራዊት እና የብሄራዊ ፓርኮች ጥበቃ ባለሥልጣናት ከህገ ወጥ አዳኞች ተወርሰው እና ከሞቱት ዝሆኖች ላይ ተነቅለው የተከማቹትን የዝሆን ጥርሶች ለአውሮፓ ህብረት አባል ሀገሮች አምባሳደሮች አስጎብኝተዋል።

ቁጥራቸው የተመናመነ የዱር አራዊት ዝርያዎች ደህንነት የሚከታተለው በምህጻር "ሳይትስ" ተብሎ የሚጠራው ዐለም አቀፍ አካል እአአ ከ1989 ጀምሮ የዝሆን ጥርስ መሸጥ የከለከለ ሲሆን ለማስፈቀድ የአውሮፓ ህብረት እና ሌሎችም ሀገሮች እንዲረዱ የዚምባቡዌ ባለሥልጣናት ተማጽነዋል።

ዚምባቡዌ አንድ መቶ ሰላሳ ቶን የዝሆን ጥርስ እና ወደሰባት ቶን የሚገመት የአውራሪስ ቀንድ ክምችት አላት ።

በቅርቡም ዚምባቡዌ አስራ አራት የአፍሪካ ሀገሮች እንዲሁም ቻይና እና ጃፓን መልዕክተኞች የሚካፈሉበት "የዝሆኖች ጉዳይ ጉባኤ" ታስተናግዳለች። ተሰብሳቢዎቹ ስለዝሆን መንጋዎች አያያዝ እንደሚወያዩ ተገልጿል።

የዝሆኖች ቁጥር በዐመት በአምስት ከመቶ በአደገኛ ሁኒታ እየጨመረ መሆኑን የምትገልጸው ዚምባብዌ አሁን ያሏት 100,000 ዝሆኖች ብሄራዊ ፓርኮቹዋ አቅም ከሚችለው በዕጥፍ የሚበልጥ መሆኑን የዱር አራዊት ጥበቃና ፓርክ ባለሥልጣናት አሳስበዋል። የዝሆን መንጋው የፓርኮቹን ዛፎች እና ቁጥቋጦ እያወደመ መሆኑንም ይናገራሉ።

ኬንያን ጨምሮ ሌሎች የአፍሪካ ሀገሮች በበኩላቸው ዓለም አቀፍ ንግድ እንዳይበረታታ የዝሆን ጥርስ ንግድ ሙሉ በሙሉ መከልከል አለበት ብለዋል።

XS
SM
MD
LG