ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን የመሥሪያ ቤታቸውን የዘጠኝ ወራት እቅድ አፈፃፀም ሪፖርት ለተወካዮች ም/ቤት ባቀረቡበት ወቅት በሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ምክንያት ሻክሮ የነበረው የኢትዮጵያና የምዕራባውያን ግንኙነት በመሻሻል ላይ እንደሚገኝ ገልፀዋል።
“መንግሥት የሰብዓዊ ድጋፍ አቅርቦት ወደ ትግራይ ክልል እንዲገባ ምቹ ሁኔታ በመፍጠሩ፣ ችግሮችን በሰላም ለመፍታት የሚያስችል እርምጃ በመውሰዱ እና መሰል ተግባራት ምክንያት ከምዕራባውያን ጋር መተማመን እየተፈጠረ ይገኛል” ብለዋል።
ይሁን እንጂ ከሰብዓዊ ድጋፍ አቅርቦት ጋር በተያያዘ መሻሻሎች ቢኖሩም፣ አሁንም ችግሮች እንደሚስተዋሉ የተለያዩ አካላት በመግለጽ ላይ ናቸው።
ለሰብዓዊ ድጋፍ አቅርቦቱ ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር በሚል፣ ህወሃት ከአፋር ክልል ታጣቂዎቹን ሙሉ በሙሉ ማስወጣቱን የሚገልጹት የክልል አመራሮች በበኩላቸው ለችግሩ ተጠያቂ የሚያደርጉት የፌዴራሉን መንግሥት ነው፡፡
ሆኖም በአሁኑ ወቅት ወደ ክልሉ እየገባ ያለው እርዳታ ተስፋ ሰጭ መሆኑን ለአሜሪካ ድምፅ የተናገሩት የትግራይ ክልል የግብርናና ገጠር ልማት ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር አትንኩት መዝገቡ መጠኑ ግን እጅግ አነስተኛ መሆኑን መግለፃቸው ይታወሳል።
እንደ ዓለም ምግብ ፕሮግራም እና ዩኤስኤአይዲ ያሉ ዓለም አቀፍ ለጋሽ ድርጅቶችም በመንግስት በኩል ምቹ ሁኔታ ከመፍጠር አንጻር መሻሻሎች መኖራቸውን እና ወደ ትግራይ ክልል የሚገባው የድጋፍ አቅርቦት መጨመሩን ገልጸው፣ ሁኔታዎች ይበልጥ መሻሻል እንዳለባቸው ማመልከታቸው ይታወቃል፡፡
ዝርዝሩን ከተያያዘው የድምፅ ፋይል ይከታተሉ።