የድርጅቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም በሁለተኛው ዩናይትድ ስቴትስ መሪነት የተዘጋጀ ዓለም አቀፍ ጉባዔው ባደረጉት ንግግር በዓለም ዙሪያ በኮቪድ-19 የሚያዙ እና ለህልፈት የሚዳረጉ ሰዎች ቁጥር የቀነሰ ቢሆንም ወረርሽኙ ገና አልተወገደም፣ በሁሉም ቦታ ሳይወገድ ብቻውን ሊያበቃ የሚችልበት ስፍራ ሊኖር አይችልም ብለዋል፡፡
ከሰባ በሚበልጡ ሀገሮች እንዲያውም የቫይረሱ ተጋላጮች ቁጥር እየጨመረ ነው የሚመረመሩ ሰዎች ቁጥርም እየቀነሰ ነው ብለዋል፡፡
ክትባትን በሚመለከትም ዝቅተኛ ገቢ ባላቸው ሀገሮች ከአንድ ቢሊዮን በላይ ያልተከተቡ ሰዎች እንዳሉ ነው ዶ/ር ቴድሮስ ያመለከቱት፡፡
በሌላ ዜና በአፍሪካ የኮቪድ-19 ክትባት እንዲያመርት ፈቃድ በማግኘት የመጀመሪያ የሆነው የመድሃኒት ፋብሪካ የመጣለት የክትባት ትዐዛዝ ባለመኖሩ የተነሳ በቅርቡ መዘጋቱ እንደማይቀር ኒው ዮርክ ታይምስ ዘገበ።
ደቡብ አፍሪካው አስፐን ፋርማኬር ክትባቶቹን ማምረት ፈጽሞ እንዳልጀመረ ነው ዘገባው ያመለከተው፡፡
ኩባኒያው ከዩናይትድ ስቴትሱ ጆንሰን ኤንድ ጆንሰን ጋር የኮቪድ-19 ክትባት ለማምረት ውል ተፈራረመ ተብሎ ባለፈው ዓመት ዜናው ሲሰማ አፍሪካ ላለባት የክትባት እጥረት መፍትሄ ተገኘ ተብሎ በስፋት መወራቱ አይዘነጋም፡፡