ባለፈው ሚያዚያ 18 በጎንደር ከተማ ለበርካቶች ህይወት መጥፋት፣ ንብረት መውደም እና ዘረፋ ምክንያት የሆነው ግጭት አስተዳደራዊ መሆኑን የኢትዮጵያ ኃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ገለፀ።
ከአዲስ አበባ ጎንደር የሄደው የልኡካን ቡድን ትናንት ሕዝባዊ ውይይት ያካሄደ ሲሆን ግጭቱ በመልካም አስተዳደር ችግሮች ምክኒያት የተቀሰቀሰ ስለመሆኑ ከውይይቱ የተገኘው ሐሳብ እንደሚያስረዳ የኢትዮጵያ ኃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጠቅላይ ጸኃፊ ሊቀ ትጉሃን ቀሲስ ታጋይ ታደለ ለአሜሪካ ድምጽ ገልፀዋል።
ድብቅ አጀንዳ ያላቸው ቡድኖች ይህንንም ችግር እንደ አንድ መሳሪያ በመጠቀም ግጭቱን ስለማባባሳቸው በውይይቱ ላይ መነሳቱን ምክር ቤቱ ገልጾልናል።
ከውይይቱም በኋላ በዚህ ግጭት ውስጥ በመሳተፍ፣ በመግደል በመዝረፍና ሌሎችንም ጥፋቶች በመፈፀም የተጠረጠሩ በሙሉ ለፍድር እንዲቀርቡ፣ ተጎጂ የኅብረተሰብ ክፍሎች አስፈላጊው ድጋፍ እንዲደረግላቸውና በአካባቢው የሕግ የበላይነት እንዲረጋገጥ መወሰኑን ምክር ቤቱ አስታውቋል።
የከተማዋ አስተዳደር እስካሁን በድርጊቱ ላይ ተሳትፎ አድርገዋል ተብለው የተጠረጠሩ 250 የሚደርሱ ሰዎችን በቁጥጥር ስር እንዳዋለ ገልጿል።
የኢትዮጵያ ኃይማኖት ተቋማት ጉባኤ አመራሮችን፣ የጎንደር ከተማ ከንቲባ እና የከተማዋን ነዋሪዎች ያነጋገረው ዘጋቢያችን መስፍን አራጌ ነው።