በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የዩናይትድ ስቴትስ ም/ቤት ለዩክሬን የ40 ቢሊዮን ዶላር ተጨማሪ ዕርዳታ አጸደቀ


የዩናይትድ ስቴትስ የተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ናንሲ ፐሎሲ፤ የዩናይትድ ስቴትስ የተወካዮች ምክር ቤት አባላት በሩሲያ ዩክሬን ጉዳይ
የዩናይትድ ስቴትስ የተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ናንሲ ፐሎሲ፤ የዩናይትድ ስቴትስ የተወካዮች ምክር ቤት አባላት በሩሲያ ዩክሬን ጉዳይ

የዩናይትድ ስቴትስ የተወካዮች ምክር ቤት ለዩክሬን ከአርባ ቢሊዮን ዶላር በላይ ተጨማሪ ዕርዳታ እንዲሰጥ ትናንት ማክሰኞ አጽድቆታል። ምክር ቤቱ የዩክሬን ድጋፍ ወጪ ህጉን በ368 አባላት ድጋፍ ሲያሳልፍ 57 አባላት ተቃውመዋል።

የተቃወሙት ሁሉም ሪፐብሊካን አባላት ናቸው። ረቂቅ ህጉ ወደመወሰኛው ምክር ቤት የሚመራ ሲሆን ባፋጣኝ ድምፅ ይሰጥበታል ተብሎ ይጠበቃል።

ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን የዩናይትድ ስቴትስ ምክር ቤት ለዩክሬን የሰላሳ ሦስት ቢሊዮን ዶላር ተጨማሪ ዕርዳታ እንዲፈቅድ የጠየቁ ሲሆን የምክር ቤት አባላቱ ሰባት ቢሊዮን ዶላር ጨምረው ረቂቅ ህጉን አሳልፈዋል።

ፕሬዚዳንት ባይደን አሁን ያለው የዩክሬን እርዳታ በዚሁ በግንቦት ወር ውስጥ ከማብቃቱ አስቀድሞ ምክር ቤቱ ፈጥኖ ህጉን እንዲልክላቸው እና እንዲፈርሙት መጠየቃቸው ይታወሳል።

አንዳንድ ሪፐብሊካን የምክር ቤት አባላት ዲሞክራቶቹ የግብር ከፋዩን ገንዘብ ወደውጪ ለመላክ ከመጠን ተጣደፉ በማለት ረቂቅ ህጉን ተቃውመዋል። የፕሬዚዳንቱ ዲሞክራቲክ ፓርቲ አባላት ምክር ቤቱን በጠባብ ብልጫ እየመሩ ሲሆን ረቂቅ ህጉ በመወሰኛ ምክር ቤት ለማለፍ የሪፐብሊካኖች ድጋፍ ያስፈልገዋል።

በውጊያው ግንባር -

የዩክሬን ባለሥልጣናት ኃይሎቻቸው የሩሲያን ወታደሮች ከሰሜን ምስራቋ ኻርኪቭ ከተማ ገፍተው በማስወጣት ድል እያስመዘገቡ መሆናቸው ተናገሩ።

ኻርኪቭ ሩሲያ ወረራውን ከከፈተችበት ጊዜ አንስታ ስትደበድባት የቆየችው ከተማ መሆኗ ተገልጿል። የዩክሬን ፕሬዚዳንት ቮሎዶሚር ዜሌንስኪ ወራሪው ቀስ በቀስ እየተባረረ ነው ብለው ሆኖም ከመጠን በላይ ስሜታዊ ሆነን በሰራዊታችን በየሳምንቱ ወይም በየቀኑ ድል በመጠበቅ ከልክ ያለፈ ግፊት የሚያደርግ ድባብ መፍጠር የለብንም ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

ትናንት የሩሲያ ኃይሎች ኦዴሳ ከተማ ላይ ሰባት ሚሳይሎች መተኮሳቸውን የዩክሬን ባለሥልጣናት ገልጸዋል።

XS
SM
MD
LG