በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ጨዋታዎችን በሜዳዋ ማድረግ እንደማትችል ካፍ አስታወቀ


CAF logo
CAF logo

የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በጻፈው ደብዳቤ፣ ኢትዮጵያ ለቀጣዩ የአፍሪካ ዋንጫ በሜዳዋ የማጣሪያ ጨዋታዎችን የማከናወን ፍቃድ እንዳላገኘች መግለጹን ፌዴሬሽኑ አስታውቋል፡፡

ካፍ የውሳኔ ደብዳቤውን ለፌዴሬሽኑ የጻፈው፣ ባለፈው ሐሙስ ሚያዝያ 27 የባህር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየምን ውድድሮችን የማስተናገድ አቅም በባለሙያ ማስገምገሙን ተከትሎ ነው፡፡

ኢትዮጵያ በሀገሯ የምታካሂዳቸውን ዓለም አቀፍ ውድድሮች የምታስተናግድባቸው ስታዲየሞች የካፍን መመዘኛዎች እንደማያሟሉ በመግለጽ ካለፈው ጥቅምት ወር ጀምሮ እገዳ እንደተጣለባቸው ይታወሳል፡፡

ይህን ተከትሎ በተለይ የባህር ዳር ስታዲየምን ደረጃ ለማሻሻል የተለያዩ ሥራዎች ሲሰሩ መቆየታቸውን የገለጸው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን፣ ባለፈው ሳምንት ሚስተር ኢቫን ኪንቱ የተባሉ የካፍ ባለሙያ በስታዲየሙ ተገኝተው የተደረጉ ማሻሻያዎችን መገምገማቸውን አመልክቷል፡፡

እኚህ ኡጋንዳዊ የካፍ ባለሙያ ያቀረቡትን የግምገማ ሪፖርት መነሸ በማድረግ፣ ስታዲየሙ አሁንም ድረስ መመዘኛዎቹን እንደማያሟላ በመግለጽ፣ ካፍ ባለፈው ጥቅምት ወር ያሳለፈውን ውሳኔ ማጽናቱን ፌዴሬሽኑ ዛሬ ከሰዓት በኋላ በድረገጹ ባወጣው ሪፖርት ይፋ አድርጓል፡፡

ፌዴሬሽኑ፣ ካፍ ላከልኝ ባለው ባለ ሰባት ገጽ ደብዳቤ፣ ከፍተኛ መዋዕለ ነዋይ የሚጠይቁ እና መሟላት አለባቸው የተባሉ 10 የተለያዩ መመዘኛዎች ላይ ድምዳሜውን ማስቀመጡን ነው የገለጸው፡፡

ከነዚህም መካከል፣ የመጫወቻ ሜዳው በአዲስ የተፈጥሮ ሳር እንዲተካ፣ አውቶማቲክ የውሃ ማጠጫ እንዲኖረው፣ የካፍ መመዘኛን የሚያሟላ የስታዲየም ፓውዛ እንዲኖረው፣ የመልበሻ ክፍሎች ሙሉ በሙሉ በአዲስ መልክ እንዲሰሩ የሚሉ እና ከመጫወቻ ሜዳው፣ ከመልበሸ፣ ከሜዲካል እና ከሚዲያ ክፍሎች እንዲሁም ቪአይፒን ጨምሮ ከተመልካች ስፍራ እና የልምምድ ቦታ ጋር የተያያዙ በርካታ ማሻሻያ የሚፈልጉ ነጥቦች ተዘርዝረዋል፡፡

ይህን ጉዳይ በተመለከተ ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝደንት፣ እንዲሁም ከፌዴሬሽኑ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም፡፡

እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ለ2023 የአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ ድልድል በምድብ አራት ኢትዮጵያ ከግብፅ፣ ጊኒ እና ማላዊ ጋር የተደለደለች ሲሆን፣ የተባሉት ማሻሻያዎች ተደርገው ካፍ ውሳኔውን እስኪቀይር፣ ኢትዮጵያ በማጣሪያው ከግብፅ ጋር የምታደርገውን ሁለተኛ ጨዋታ ጨምሮ በቀጣይ በሜዳዋ ታደርጋቸው የነበሩ የማጣሪያ እና ሌሎች ዓለም አቀፍ ጨዋታዎችን በገለልተኛ ሀገር ሜዳ ለማድረግ ትገደዳለች፡፡


ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ጨዋታዎችን በሜዳዋ ማድረግ እንደማትችል ካፍ አስታወቀ
please wait

No media source currently available

0:00 0:02:33 0:00

XS
SM
MD
LG