የጀርመን የመከላከያ ሚንስትር ማሊ ሞራ ውስጥ ከተፈጸመው የጭካኔ አድራጎት በኋላ የጀርመን የጦር ኅይል ማሊ የመቆየቱ ጉዳይ እንደሚያጠራጥራቸው በድጋሚ አስታወቁ።
ሚንስትር ክሪስቲን ላምብሬክት ይህን ያስታወቁት በትናንቱ የማሊ ጉብኝታቸው ባደረጉት ንግግር ሞራ መንደር ውስጥ የደረሰውን አንስተው ሲናገሩ ነው።
የማሊ መንግሥት ሞራ ውስጥ 203 ሽብርተኞችን ደምሥሰናል ቢልም የዜና ተቋማት እና ሂዩማን ራይትስ ዋች ያነጋገሯቸው የዐይን ምስክሮች ግን የመንግስት ወታደሮች ብዛት ያላቸው ሰላማዊ ሰዎችን እንደገደሉ ገልጸዋል።
ላምብሬኽት ሰሜን ጋዎ የሚገኙ የጀርመን ወታደሮችን ካነጋገሩ በኋላ እንዲህ ላለ አገዛዝ ድጋፍ መስጠት እንፈልጋለን ወይ ? የሚል ጥያቄ ማንሳታቸውን ከሚኒስቴራቸው የወጣ መረጃ አመልክቷል።
"እጅግ የላቀ ብቃት ያላቸው የጀርመን ወታደሮች የሚያሰለጥኗቸው የማሊ ወታደሮች ይህን ብቃታቸውን ይዘው - ከሩስያ ኃይሎች ቅጥረኛ ወታደሮች ጋር ይሰማራሉ - ያሉት የጀርመን የመከላክያ ሚንስትር ላምብሬኽት - በተለይም ሞራ ላይ ከተፈጸመው ተግባር በኋላ ከእኛ እሴቶች ጋር ይጣጣማል ወይ የሚል ጥያቄ የሚያስነሳ ነው" ማለታቸው ተዘግቧል።