በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የትግራይ ክልል የተባለው እርዳታ እየደረሰ አይደለም አለ


በኢትዮጵያ ትግራይ መቀሌ ከተማን የሚያሳይ ምስል/ እንደ አውሮፓውያን የቀን አቆጣጠር በጥር 5/2020 ዓ/ም / ፎቶ ኤድዋርዶ ሶተረስ/ ኤ.ኤፍ.ፒ/
በኢትዮጵያ ትግራይ መቀሌ ከተማን የሚያሳይ ምስል/ እንደ አውሮፓውያን የቀን አቆጣጠር በጥር 5/2020 ዓ/ም / ፎቶ ኤድዋርዶ ሶተረስ/ ኤ.ኤፍ.ፒ/

ለትግራይ ክልል ሕዝብ አስቸኳይ የምግብ እርዳታ ለማድረስ ከሁለት ሳምንት በፊት የተደረገውን የተናጥል የተኩስ አቁም ስምምነት ተከትሎ ወደ ክልሉ የገቡ እርዳታ የጫኑ ተሽከርካሪዎች ቁጥር 26 ብቻ መሆናቸውን ክልሉ በዛሬው ዕለት "ትግራይ የውጭ ጉዳይ ቢሮ" እያለ በሚጠራው የትዊተር ገፅ ላይ ባወጣው መግለጫ አስታወቀ።

መግለጫው አክሎም የኢትዮጵያ መንግሥት “ግጭት የማቆም ስምምነቱን አጋጣሚ የትግራይን ህዝብ እርዳታ እንዳይደርስ ለሚያራምደው የጭካኔት ተግባሩ የተጠቀመበት ለመሆኑ ማረጋገጫ ነው” ብሏል፡፡

የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ወደ ትግራይ እየገባ ያለው ሰብአዊ እርዳታ በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ መሆኑን በሚያወጡት የሐስት መግለጫ በተደጋጋሚ የሚናገሩ ቢሆንም እውነታው ግን ከዚህ የተለየ መሆኑን መግለጫው አመልክቷል፡፡

አንዳንድ ዓለም አቀፍ የረድኤት ድርጅቶችም ያለባቸው የሕግ የሞራልና የሞያ ግዴታ ወደ ጎን በማለት ወደ ትግራይ የሚገባው እርዳታ እየጨመረ መሆኑን በመግለጽ ለኢትዮጵያ መንግሥት የሀሰት ትርክት ያስተጋባሉ በማለት መግለጫው በስም ያለያቸውን የረድኤት ድርጅቶች ተችቷል።

መግለጫው አያይዞም የትግራይ መንግሥት በትግራይ ህዝብ ህይወት ላይ የሚካሄደውን እንዲህ ያለው ቀልድ እንዲቆምና ሰው ሰራሽ የሆነው የሰብአዊ እርዳታ እገዳ እንዲያበቃና የተቋረጡት መሠረታዊ ማህበራዊ አገልግሎቶች እንዲመለሱ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ግፊት እንዲያደርግ ጠይቋል፡፡

ይህን መግለጫ ተከትሎ እስካሁን በኢትዮጵያ መንግሥት በኩል የተባለ ነገር የለም። ሆኖም የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትሩ ዶ/ር ለገሰ ቱሉ ሰሞኑን ለአሜሪካ ድምፅ በሰጡት ማብራሪያ "የተጀመረውን የእርዳታ አቅርቦት ማቀላጠፍ እንዲቻል፣ የሕወሓት ታጣቂዎች ከያዟቸው የአፋር ክልል አካባቢዎች ለቀው መውጣት አለባቸው ከካሉት በተጨማሪ፣ ወደ ክልሉ የገቡ የጭነት ተሸከርካሪዎች ጭነታቸውን እንዳራገፉ መመለስ አለባቸው" ማለታቸው ይታወሳል።

XS
SM
MD
LG