በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በአባ ገዳዎች ላይ ታጣቂዎች ጥቃት እየፈፀሙ ነው ተባለ


በአባ ገዳዎች ላይ ታጣቂዎች ጥቃት እየፈፀሙ ነው ተባለ
please wait

No media source currently available

0:00 0:03:24 0:00

በአባ ገዳዎች ላይ ታጣቂዎች ጥቃት እየፈፀሙ ነው ተባለ

የጅማ አርጆ ወረዳ አባ ገዳዎች ኅብረት ሰብሳቢ አባ ገዳ ራሻ ማርቆስ ባለፈው ዕሁድ በታጣቂዎች መገደላቸውን የወረዳው አስተዳዳሪ ለአሜሪካ ድምፅ ገልፀዋል።

ከሁለት ሳምንት በፊትም በአባ ገዳ ራሻ መኖሪያ ቤት ላይ ጥቃት መፈፀሙንና ተጠርጣሪዎቹ መንግሥት “ሸኔ” የሚላቸው እራሳቸውን “የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት” ብለው የሚጠሩ ሸማቂዎች መሆናቸውን አባ ገዳዎች ተናግረዋል።

የታጣቂዎቹ የውጭ ቃል አቀባይ መሆናቸውን የገለፁ ግለሰብ ደግሞ ክሱን አስተባብለዋል።

በምስራቅ ወለጋ ዞን ውስጥ የጅማ አርጆ ወረዳ አባ ገዳዎች ኅብረት ሰብሳቢ ራሻ ማርቆስ መጋቢት ቅዳሜ መጋቢት 24/2014 ዓ.ም ለሊት በታጣቂዎች ተገድለው ሰኞ መጋቢት 26/ 2014 ዓ.ም መቀበራቸውን የወረዳው አስተዳዳሪ አቶ ጋሻሁን ታከለ ለአሜሪካ ድምፅ ተናግረዋል።

"ኦነግ ሸኔ የተባለው ታጣቂ ቡድን በሌሊት ከመኖሪያ ቤታቸው በማሰወጣት የቤተሰቦቻቸውን አባላት እንዳይከተሏቸው እንዲመለሱ በማድረግ ደብድበውና ጀርባቸውን ወግተው ገድለዋቸዋል"

በሌላ በኩል የኦሮሞ አባ ገዳዎች ኅብረት ጸሐፊና የጉጂ አባ ገዳ ጅሎ ማንዶ ከሁለት ሳምንት በፊት ለሊት ላይ ሸኔ ሲሉ የጠሯቸው ታጣቂዎች በመኖሪያ ቤታቸው ብዙ ጥይት እንደተተኮሰባቸው ተናግረዋል።

"የተኮሱትን ጥይት ከመሬት ሰብስበን ስንቆጥረው 47 ሆነ። በአራት ሞተርሳይክል ስለመጡ ስንት እንደሆኑ አናቅም።” ካሉ በኋላ “ቤት ውስጥ የነበሩ 12 ሰዎችን በተኩሱ አልተጎዱም ነገር ግን ቤቱ ተሰባበረ እንዲሁም ቤት ውስጥ የነበረ የቡና ክምር ተበተ።” ብለዋል። አያይዘውም “በወቅቱ ታጣቂዎቹ እኛ "ወቦ" ነን። እናንተ የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊትን በትናችኋል። ጠላት ናቸሁ እያሉ ተኩስ ከፍተው ነው የሄዱት" ብለዋል።

የኦሮሞ አባ ገዳዎች ኅብረት ፀሐፊና የቱለማ አባ ገዳ ጎበነ ሆላ "ሸማቂዎቹም ሆኑ የመንግስት ጸጥታ ኃይሎች የገዳ ሥርዓትን ምንነት ለይተው ባለማወቃቸው አባ ገዳዎች ላይ ጥቃት ይፈጽማሉ" ሲሉ ተናግረዋል።

"ሁለቱ ተፋላሚ ኃይሎች ሊገነዘቡት የሚገባው ጠፍቶ ለማጥፋት ካልሆነ በስተቀር በጦርነት መፍትሄ ያሰገኘች አገር የለችም።” ያሉት አባ ገዳ ጎበነ ሆላ “ስለዚህ የኦሮሞ ሕዝብ ስላለው ችግር አስተውሎ ቢያይና ያለውም ችግር በውይይት ቢፈታ ይሻላል ነው የምለው።" ብለዋል።

በዚህ ዙርያ መንግሥት ሸኔ የሚላቸው እራሳቸውን የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት ብለው የሚጠሩ ሸማቂዎች ቡድን ዓለም አቀፍ ቃል አቀባይ መሆናቸውን የተናገሩት አቶ ኦዳ ተርቢ "የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት ታዋቂ የሆኑ ግለሰቦች ላይ እርምጃ እንደሚወስድ መንግስት በተለያዩ ጊዜያት የሚገልጸው በህብረተሰቡና "ወቦ" መካከል ችግር ለመፍጠር ነው። ሰራዊቱ የጅማ አርጆ አባ ገዳን አልገደለም። በተከበሩ አባ ገዳ ጅሎ ማንዶ መኖሪያ ቤትም ላይ ተኩስ አልከፈተም" ሲሉ በስልክ ምላሽ ሰጥተዋል።

በካማሺ የማረሚያ ፖሊስ አዛዦችም ላይ ሸማቂ ቡደኑ እገታ አልፈጸም ያሉት አቶ ኦዳ ተርቢ "መንግሥት የወቦን ስም እያጠለሸ ነው" ሲሉ አክለው ገልጸዋል።

በዚህ ጉዳይ ላይ ወቀሳ ያቀረበው መንግሥት ብቻ ሳይሆን አባ ገዳዎቹም መሆናቸውን ጠቅሰን የጠየቅናቸው አቶ ኦዳ “ጥፋት የሚፈፅም ሰው እራሱን አያጋልጥም። ይህ በምክኒያት የሆነ ነው። ይህ ማለት ወደ አባ ገዳ ጅሎ ማንዶ ቤት በመሄድ ተኩሶባቸው እኛ ወቦ ነነ የሚል ታጣቂም ቢሆን የመንግሥት እቅድ ነው። ወቦና ሕዝቡን ለማለያየት እንጂ ከኛ ጋር የሚያያዝ ድርጊት አይደለም” ሲሉ መልሰዋል።

አስተያየት ሰጪዎቹ (ወቦ) እያሉ በምፅሃረ ቃሉ የሚጠሩት ወራነ ቢሊሱማ ኦሮሞ ሲሆን የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊትን ማለት ነው።

የኦሮምያ ክልል መንግሥት ከዚህ ቀደም ከታጣቂዎቹ ጋር ምንም ዓይነት ድርድር እንደማይኖርና ታጣቂዎቹ በሰላማዊ መንግድ እጃቸውን እየሰጡ እንዲገቡ ጥሪ ማቅረቡን እንዲሁም በርካታ የሸማቂ ቡድኑ አባላትም እጃቸውን እየሠጡ ሲገቡ እንደነበር ሲገልፅ ቆይቷል።

XS
SM
MD
LG