በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የተራራ ኔትወርክ ዋና አዘጋጅ ታምራት ነገራ በዋስ እንዲለቀቅ ፍ/ቤት ትዕዛዝ ሰጠ


ፎቶ ፋይል ፡ ታምራት ነገራ ኅዳር/ 2008 ዓ. ም. በዩናይትድ ስቴትስ ሜሪላንድ/ ሰባት ኪሎ የተሰኘ መጽሔት ምርቃት ሥነስርዓት ላይ
ፎቶ ፋይል ፡ ታምራት ነገራ ኅዳር/ 2008 ዓ. ም. በዩናይትድ ስቴትስ ሜሪላንድ/ ሰባት ኪሎ የተሰኘ መጽሔት ምርቃት ሥነስርዓት ላይ

ላለፉት አራት ወራት በእስር ላይ የነበረው የተራራ ኔትወርክ የኢንተርኔት ላይ ሚዲያ ዋና አዘጋጅ ታምራት ነገራ በ50 ሺሕ ብር ዋስ ከእስር እንዲፈታ የኦሮሚያ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፍርድ ቤት ወሰነ።

ዛሬ መጋቢት 27 ቀን 2014 ዓ.ም የተሰየመው የኦሮምያ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ጠበቃው ያቀረቡትን የዋስትና ጥያቄ ከመረመረ በኋላ ታምራት ነገራ 50 ሺሕ ብር የገንዘብ ዋስትና አስይዞ ከእስር እንዲወጣ ውሳኔ መስጠቱን ጠበቃው አቶ ገመቹ ጉተማ ለአሜሪካ ድምፅ ገልፀዋል።

ታምራት ነገራን ፖሊስ “በሽብር ወንጀል እጠረጥረዋለሁ” በማለቱ ከታኅሣሥ 1 ቀን 2014 ዓ.ም ጀምሮ በእስር ላይ እንደሚገኝ አቶ ገመቹ ጉተማ ተናግረዋል። እስከ ዛሬም እስር ቤት ነው ያለው።

“በሽብር ለተወነጀሉ ወይም አሸባሪተብለው ለተፈረጁ አካላት በሚዲያ አማካኝነት ይረዳ ነበር” በሚል የጥርጣሬ ክስ ፍርድ ቤት ሲመላለስ መቆየቱን ጠበቃው ተናግረዋል።

ታምራት ነገራ መጋቢት 1 ቀን 2014 ዓ.ም በገላን ከተማ ወረዳ ፍርድ ቤት ሲቀርብ ፤ ዓቃቤ ሕግ በ15 ቀናት ውስጥ ክስ እንዲመሰርት ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ ሰጥቶ እንደነበር አቶ ገመቹ አስታውሰዋል።

አቶ ገመቹ የደንበኛቸው ታምራት የዋስ መብት እንዲከበር ለኦሮሚያ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ጥያቄ ያቀረቡት መጋቢት 1/2014 ዓ.ም መሆኑን ገልፀው ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ በተደጋጋሚ ቅሬታ ያቀርብ እንደነበር ገልፀዋል።

ጠበቃው የነበረውን የፍርድ ሂደት ሲያስታውሱ፤

“የዋስትና መብት እንዲጠበቅለት ለኦሮምያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ቀረበ። አቃቤ ሕግ በጉዳዩ ላይ መልስ እንዲሰጥም ታዘዘ። ዓቃቤ ሕግም የዋስትና መብትን በመቃወም ያቀረበው መቃወሚያም፤ የጦር መሳሪያ ታጥቀው ያመፁና የእርስ በእስር ጦርነት ለማስነሳት በመንግሥት ላይ ወንጄል የፈፀሙ አካላት በመደገፍ፣ በመሳተፍና ሚዲያውን በመጠቀም ህወሓት እና ኦነግ ሸኔ የአሸባሪነት ወንጄል እየፈፀሙ በመንግሥት ላይ ጦርነት በከፈቱ ግዜ ተሳትፎ እያደረገ ነበር የሚል የሚል ይገኝበታል” ብለዋል።

አያይዘውም “የኦሮምያ ክልል መንግሥት ሙሉ በሙሉ መፍረስ አለበት ብለው በሚንቀሳቀሱ አካላት ውስጥ የተሳተፈ መሆኑን የምርመራ መዝገቡ ያሳያል። ስለዚህ ይህ ወንጀል ከባድ በመሆኑ የዋስት መብት አይፈቀድለትም የሚል መቃወሚያ በአቃቤ ሕግ በኩል መጋቢት 2 የቀረበውን መቃወሚያ ፍርድ ቤቱ ሲመረምር ቆይቶ ነው ዛሬ ውሳኔ የሰጠው” ብለዋል አቶ ገመቹ።

ደንበኛቸውን በተመለከተ ያቀረቡት የዋስትና ጥያቄ በተከታታይ በተሰጡ አራት ቀጠሮች ሳይወሰን መቆየቱን አስታውሰው በመጨረሻ ግራ ቀኙን ሲያዳምጥ የቆየው የኦሮምያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዛሬ መጋቢት 27 ቀን 2014 ዓ.ም ተጠርጣሪው 50 ሺሕ ብር ዋስትና አስይዞ ከእስር እንዲቀጣ ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ ሰጥቷል።

ጋዜጠኛ ታምራት ነገራ የፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ እስኪፈፀም በሰበታ ከተማ ዳላቲ ፖሊስ ጣብያ ውስጥ ይህ ዘገባ እስከተላለፈበት ግዜ ድረስ ታስሮ እንደሚገኝ ጠበቃው አቶ ገመቹ ለአሜሪካ ድምፅ ተናግረዋል።

XS
SM
MD
LG