በኢትዮጵያ በርካታ መጽሃፍት ቤቶችን የገነባው እና የንባብን ባህል ለማሳደግ እየጣረ የሚገኘው ኢትዮጵያ ሪድስ አጋር መስራች ጄን ከርትዝ ዓለም አቀፉ ለወጣቶች የተጻፉ መጽሃፍት ቦርድ (IBBY) ያዘጋጀው ሽልማት አሸናፊ መሆናቸው ከሰሞኑ ይፋ ተደርጓል።
የኢትዮጵያ ትዝታቸውን ጨምረው ከ40 በላይ የህጻናት መጽሐፍቶችን ያሳተሙት ጄን የላቀ ንባብ ባህልን በማጎልበት ረገድ ላበረከቱት፣ ዓመታትን ለተሻገረ አስተዋጽኦቸው ሽልማቱ እንደተሰጣቸው ታውቋል። በቀጣዩ አጭር ዘገባ ፣ ሀብታሙ ስዩም ስለ ደራሲዋ፣ መምህርቷ፣ እና የንባብ ባህል አስፋፊዋ ጄን ከርትዝ በጥቂቱ ይነግረናል።
የሁለተኛው የዓለም ጦርነት አሰቃቂ ትዕይንቶች ስለ ዓለም ያላቸውን እይታ ከለወጠባቸው የወቅቱ የአሜሪካ ወጣቶች መካከል አንዱ ሀሮልድ ከርትዝ ናቸው። ከወንድሞቻቸው ጋር በጦር አውሮፕላን አብራሪነት በአውሮፓ የቆዩት ሀሮልድ ፣ ወደ ሀገራቸው ዩናይትድ ስቴትስ ከተመለሱ በኃላ ፣ለዓለም መልካም የሚያበረክቱበትን አፍታ ሲጠባበቁ የቆዩ ይመስላሉ። ለዚያ ሳይሆን አይቀርም በወቅቱ የኢትዮጵያ ንጉስ የነበሩትን ቀደማዊ ኃይለስላሴን ጥሪ ተቀብለው፣ በተለያዩ ዘርፎች ባለሙያዎችን ወደ ምትሻው ኢትዮጵያ ከባለቤታቸው ፓውሊን ከርዝ እና ልጆቻቸው ጋር ጠቅልለው ያቀኑት።
ከቤተሰቡ አባላት መካከል የሁለት አመቷ ጄን ከርዝ ትገኝበታለች ። በፖርት ላንድ ኦሪገን የዛሬ 69 ዓመት የተወለዱት ጄን ፣ ልጅነታቸውን ሲያስታውሱ እንዲህ ይላሉ፣ “ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ብወለድም ፣ ከኢትዮጵያ የተነጠለ ትዝታ ግን የለኝም ።ህጻን እያለሁ በየአምስት ዓመቱ ከቤተሰቦቼ ጋር አሜሪካን እንጎበኝ ነበር። በሰባት አመቴ ወደ ቦይሲ አይዶዋ መጥቻለሁ።ከአሜሪካዊያን የትምህርት ቤት እኩዮቼ ጋር ተመሳሳይ ትወስታ ስላልነበረኝ በግራ መጋባት የታጀበ ቆይታ አሳለፍኩ ። ሕጻናቱ ስለ ኢትዮጵያ የቀደመ ዕውቀት ስላልነበራቸው ጥሩ ጥያቄ መጠየቅ እንኳ አይችሉበትም።ከኢትዮጵያ ወደ አሜሪካ የሚመጡ ሰዎች እንደሚገጥማቸው ሁሉ እኔም ፣በእኔ እና በእነሱ መካከል ያለው ክፍተት (እንግድነት) ተሰማኝ ።የልጅነት ህይወቴ እንዲያ ነበር "
ህጸኗ ጄን እና ቤተሰቦቿ ይኖሩ የነበሩት በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ በምትገኘው ማጂ ከተማ ውስጥ ነበር ። ዘመናዊ ትምህርት ቤቶች ጥቂት በነበሩበት በዚያ ዘመን ፣ ያለውን ነባራዊ ሁኔታ በማጤን ፣ የትምህርትን ጠቃሚነት የህጻን ጭንቅላታቸው እንደተረዳ ያወሳሉ ።“ባደግኩባት የደቡብ ምዕራቧ ማጂ ከተማ ዕድሉን ያገኙ የአካባቢው ልጆች የሚማሩበት አንድ ብቻ ትምህርት ቤት እንደነበረ አስታውሳለሁ ።ህጻናቱ ወደ ትምህርት ቤት ለመሄድ በመቻላቸው ምን ያህል ደስተኛ እንደነበሩ ፣ ምን ያህል የመማር ፍላጎት እንደነበራቸው ተመልክቻለሁ” ይቀጥላሉ ለአሜሪካ ድምጽ ትዝታቸውን በዙም አውታር በኩል ያከፈሉት ጄን ፣ “ በአብዛኛው ወደ ትምህርት ቤቱ የሚሄዱት ወንድ ልጆች ብቻ ነበሩ።በዚያን ወቅት ወላጆች በአብዛኛው ሴት ልጆችን ወደ ትምህርት አይልኩም ነበር ። ወደ ትምህርት ቤት ለመሄድ ፣ለማንበብ የቻልኩ ዕድለኛ ሴት ልጅ መሆኔ በወቅቱ ገብቶኛል “
የልጅነት እና የአፍላ ወጣትነት ዕድሜዋን በምስራቅ አፍሪካዊቷ ሀገር ያሳለፈችው ጄን ከኢትዮጵያ ጋር ለረጅም ዓመታት የተለያዩት ዕድሜዋ ለከፍተኛ ትምህርት ደርሶ ወደ ዩናይትድ ስቴትስ ዳግም ከአቀናች በኃላ ነው ። የኢትዮጵያ ትዝታ ግን ከወጣቷ ጄን የሚጠፋ አልነበረም ። ጭራሽኑ ብርቅ ትዝታዎቿ የጸሓፊነት ተሰጥኦዎን ቀስቀስውት በርከት ያሉ መጽሃፍትን እንድትጽፍ መነሻ ሆኗት። መጽሃፍቶቿ ትዝታ ማስታገሻ የሆኗት ይመስላሉ ፣ ተንኮለኛው ተክሌ፣ኮብላዩ እንጀራ ፣የተራራ ላይ እሳት ፣ኢትዮጵያ -የአፍሪካ ጣሪያ ሌሎችም . . . ምን መጻፍ ብቻ -ዳግም ወደ ኢትዮጵያ መመለሻም ምክንያት እንጂ። እንዴት? ጄን እንዲህ ይተርኩታል ፣“ከዓመታት በኃላ በኢትዮጵያ ውስጥ ካሰለፍኩት ልጅነቴ ጋር የተያያዙ 40 የህጻናት መጽሃፍትን ጻፍኩ። በአዲስ አበባ ውስጥ በሚገኙ ሶስት ዓለም አቀፍ ትምህርት ቤቶች ንግግር እንዳደርግ መጋበዜ ከ20 ዓመታት በኃላ ወደ ኢትዮጵያ ለመመለስ ዕድሉን ፈጠረልኝ ። ታላቅ ወንድሜ እና እህቴ በደርግ የመጨረሻ ዓመታት ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰው በአዲስ አበባ በሚገኝ የሴቶች ትምህርት ቤት መምህራን ሆነዋል ።በእኔ በኩል ወትሮውንም ከኢትዮጵያ ጋር ቁርኝት አለኝ ። ይሁንና እስከ ጎረጎሳዊያኑ 1997 ለመመለስ አልቻልኩም ነበር።ከተመለስኩ በኃላ መልካም ዕድሎች እንዳሉ ተመለከትኩ “
በዚህ ጊዜ ነበር ጄን ትልቅ ግምት የሚሰጡትን ትምህርት እና የጸሓፊነት ችሎታቸውን ያጣመረ መላ መዘርጋት እንዳለባቸው ያሰቡት ፣ “ በርካታ ሴቶች እና ወንድ ተማሪዎችን ወደ ትምህርት ቤት ለመላክ ግፊት እንዳለ አየሁ። በርካታ ትምህርት ቤቶች ግን ምንም የህጻናት መጽሃፍት የላቸውም ። ይሄ ነበር እንደ ጸሓፊ ፣ ኢትዮጵያን ፣ ማንበብ እና መጻፍ እንደሚወድ ሰው ያነሳሳኝ ።አንተ የጻፈከው፣ ሌላውም የከተበው እንዲነበብ ዕድል ትፈልጋለህ።እኛ ጸሃፊዎች በመጽሃፍት ፍቅር የወደቅን ሰዎች ነን። ይሄ ነበረ ዋነኛ የንሸጣ ምንጭ የሆነኝ። ምን እንደሚደረግ በወቅቱ አላወቅም ነበር ።ይሁንና እነዚህ ትምህርት ቤቶች ግን መጽሃፍት ሊያገኙ እንደሚገባ አመንኩ። ካለ ንባብ ትምህርት ሊኖር አይችልም ።"
የዛሬ 24 ዓመት ገደማ ነበር የመጀመሪያ ንባብ ፣ትምህርት እና መጸሃፍትን የሚመለከተው የተደራጀ እንቅስቃሴ የተጀመረው። በአጋር መስራችነት በኃላም የቦርድ አስፈጻሚ ሆነው የሰሩበት ኢትዮጵያ ሪድስ ድርጅት -ኢትዮጵያ ውስጥ በተለያዩ ስፍራዎች በርካታ መጽሃፍት ቤቶችን በማዋቀር ረገድ መልካም ስም ገንብቷል።በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ መጽሃፍትን ለህጻናት እና ቤተሰቦቻቸው አዳርሷል። ያም ቢሆን ግን ንባብ እና የህጻናት መጽሃፍት ስርጭትን በተመለከተ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ሁኔታ ጄንን ዛሬም ያረካ አይመስልም።
ከኢትዮጵያ ሪድስ የቦርድ አስፈጻሚነት ከለቀቁ በኃላ፣ ድርጅቱ በሚደግፋቸው የንባቡ ጉባኤዎች በአዲስ አበባ መሳተፍ የቀጠሉት ጄን ስለ ሁኔታው እንዲህ ያስረዳሉ፣ “በእነዚህ ስፍራዎች በእንግድነት መጋበዜ ፣ የንባብ ትምህሮቶች የፈጠሩትን ውጤት ፣ እና ትምህርት ቤቶች በምን ደረጃ ላይ እንዳሉ ለመመዘን የቻሉ ከትምህርት ሚኒስትር እና የሌሎች ትልቅ ተቋማት የመጡ ተወካዮችን ለማግኘት በእጅጉ ጠቅሞኛል ። በዚህ ሂደት የንባብ ባህል ኢትዮጵያ ውስጥ በፈጥነት እያደገ አለመሆኑን አውቄያለሁ።በእኔ ግምት ይሄ በአብዛኛው የተፈጠረው ፣ ህጻናት የሚያነቧቸው መጽሃፍት ባለመኖራቸው ነው።አንድ ሰው የሚያነበው እስከሌለ ድረስ ጥሩ አንባቢ ሊሆን አይችልም ። ዛሬ ላይ ኢትዮጵያ ሪድስን የመሰሉ ተቋማት መጽሃፍት ቤቶችን እያስፋፉ ይገኛሉ ።ቤተሰብን ማስተማር የመሰሉ መርሀ ግብሮችን በመዘርጋት ላይም አተኩረዋል ። እኔ ግን ሁላችንም መጽሃፍት ሊኖሩን ይገባል እላለሁ። ለማንበብ የሚያጓጉ መጽሃፍት ከሌሉን፣ ልጆች እንዴት ታታሪነትን በሚጠይቀው የማንበብ ክህሎት እንዲገፉ እናበረታታቸዋለን? ” ሲሉም ይጠይቃሉ።
ጄን ከርትዝ ለዓመታት ከሰሩበት ኢትዮጵያ ሪድስ ተቋም ቦረድ አስፈጻሚነት ከተለያዩ በኃላ በሌላ ግብ እና ኃላፊነት ብቅ ብለዋል ። የቅርብ ጊዜ ትኩረታቸው በኢትዮጵያ ቋንቋዎች የተዘጋጁ ባለቀለም ዐይነ ግቡ የህጻናት መጽሃፍት እንዲበራከቱ ማገዝ ላይ ሆኗል። ከልባቸው ላልጠፋችው ኢትዮጵያ የሚያበረክቱት መልካም ግብር እንደሆነም ያምናሉ።
“ አዲሱ ጥረቴ Open Hearts Big Dreams ከተሰኘ መቀመጫውን ሲያትል ካደረገ ተቋም ጋር የተሳሰረ ነው። የተወሰኑ መጽሃፍትን ኢትዮጵያ በሚነገሩ ቋንቋዎች እናዘጋጃለን። ኢትዮጵያ ሪድስ አንድ አንድ ለትርፍ ያልተቋቋመ ተቋም መጽሃፍቶቹን ወደ ኢትዮጵያ በመውሰድ ያሰራጫል ።ለምሳሌ 45ሺ ያክል መጽሃፍትን በጦርነት ለተፈናቀሉ ቤተሰቦች አከፋፍሏል። ይሄ ለኔ ትርጉም አለው።ምክንያቱም ኢትዮጵያ ውስጥ የሚሆነውን አሳዛኝ ነገር ስመለከት አቅም አልባነት ይሰማኛል ።በእነዚህ መጽሃፍት በኩል ግን በጥቂቱም ቢሆን የመልካም ተስፋ አካል እንደሆንኩ አውቃለው ።”-ብለዋል ጄን ከርዝ ።
ጄን ከርትዝ ትልቅ ስም የሚሰጠው INTERNATIONAL BOARD ON BOOKS FOR YOUNG PEOPLE (IBBY) ዓለም አቀፉ (ለወጣቶች የተጻፉ መጽሃፍት ቦርድ) –25 ዓመታትን ለተሻገረው አስተዋጽኦቸው፣ የላቀ ንባብን አበረታች በሚለው መስክ የዚህ ዓመት አሸናፊ መሆናቸውን ይፋ አድርጓል። ሸላሚው ተቋም ጄን ኢትዮጵያ ውስጥ የሀገር ውስጥ ጸሃፍት እና ሰዓሊያንን ከማገዛቸው በተጨማሪ መጽሃፍት የሚታሙበትም መሰረተ ልማት በማዋቀር ፣ መምህራን እና የቤተ መጽሃፍት ባለሙያዎች ስልጠና እንዲያገኙ በማድረግ ረገድ የነበራቸውን አስታዋጽኦ ዘርዝሯል ።
ለዚህ ክብር የበቁት ሌላዋ የህጻናት ትምህርት ባለሙያ ፣ በኢራን ገጠራማ ስፍራዎች የንባብ ባህልን ለማስፋፋት የሰሩት ዞህር ጋኒ ናቸው።በአሁኑ ጊዜ በቨርሞንት የኪነጥበብ ትምህርት ቤት በመምህርነት በማገልገል ላይ ያሉት ጄን ከርትዝ ሽለማቱ ከንባብ እና መጸሃፍት ጋር የተገናኘውን ህይወታቸውን ለዓለም ዳግም ለማጋራት ዕድል እንደሚሰጣቸው ነግረውናል።