በሚሊየኖች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዊያን ውሎ እና አዳራቸው የወትሮው ቤታቸው አይደለም ፣ እንደ ነገሩ የተሰራ ጊዜያዊ ማቆያ እንጂ።አንድ ዓመት ያስቆጠረ ጦርነት እንዲሁም ከዚያ በፊት በተለያዩ አካባቢዎች የተፈጠሩ ግጭቶች በርካታ ቤተሰቦችን አፈናቅለዋል ።የሀገሪቱ መንግስት እና ዓለም አቀፍ ተቋማት ለዕለት ፍጆታ የሚውሉ ምግብ እና መጠጥን የመሰሉ ቁሶችን ለማቅረብ ሲጥሩ ይታያል ። ኢትዮጲያ ሪድስ የተሰኘው ድርጅት ግን ለየት ባለ መልኩ ለተፈናቃይ ቤተሰቦች የሚያደርሰው ስንቅ መጽሃፍ ነው ።
እንደምን መጽሃፍት ከምግብ እና ከመጠጥ ረድፍ ተቀመጡ? የሚል ጥያቄ ከተነሳ ፣ የድርጅቱ የቦርድ ሰብሳቢ ማልኮልም ክላርክስ መልስ አላቸው ።
“ እኒህ ህጻናት ከትምህርት ርቀዋል ። በህይወታቸውም በተወሰነ መጠን ተስፋ እያጡ ነው። መፈናቀል የፈጠረባቸው የአዕምሮ መረበሽም አለ።ስለ መጪው ዘመን የሚታወቅ ነገር የለም ። ግጭቱ ተመልሶ ሊመጣም ይችላል ። ’’ ሲሉ ወቅታዊውን ሁኔታ የሚገልጹት ማልኮልም ክላርክ፣ በዚህ ፈታኝ ጊዜ ውስጥ የመጽሃፍትን ልዩ ፋይዳ ሲያስረዱ ፣“በዚህ የጭንቅ ጊዜ ጥሩ ታሪክ ያላቸው ዐይነ ግቡ መጽሃፍት የህጻናቱ ትኩረት ወደ መልካም ለመምራት ይቻላቸዋል ።የማንበብ ክህሎትን ከማሳደግ ትምህርታዊ ጠቀሜታቸው ባሻገር ፣ ወደ ሌላኛ አለም፣ ወደ ሌሎች መልካም ዕድሎች ፣ ደስታ እና ፍንደቃ ፣ ተመሰጥኦ የመውሰድ አቅም አላቸው ። ይሄ ድንቅ ነገር ይመስለኛል።” ብለዋል ።
ይሄ ለየት ያለ መርሀ ግብር ፣ በአማራ ፣ አሮሚያ እና ሶማሌ ክልል ውስጥ የሚገኙ 15ሺ ገደማ ቤተሰቦች ላይ ያነጣጠረ ነው ። ይሄን አገልግሎት ወደ ትግራይ ክልል ለማስፋፋት ፍላጎት ቢኖርም፣ በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል የተካረረው ጦርነት መሰናክል ሆኗል ።እያንዳንዱ ቤተሰብ በነፍስ ወከፍ 3 መጽሃፍት እንዲደርሱት መታለሙን፣ መጽሃፍቱም በሶስት ቋንቋች የተጻፉ እንደሆነ ፣ማልኮልም ክላርክ በስልክ ቨተደረገ ቃለምልልሳችን ወቅት ነግረውናል ።
“ ግባችን መጽሐፍቱን ማዳረስ ብቻ አይደለም ።በወላጆች (በህጻናት) መካከል የዕውቀት ሽግግር እና መነቃቃት እንዲተላለፍም ማድረግም ነው ፍላጎታችን ። ’’ የሚሉት ማልኮልም ተለቅ ያሉ ልጆች በራሳቸው ቋንቋ የተጻፉ አስደሳቾቹን በስዕሎች ያጌጡ መጽሃፍትን አንብበው የማንበብን ጥቅም በራሳቸው ጊዜ እንዲረዱ እንደሚፈልጉም ተናግረዋል ።
ዋና መቀመጫውን በዩናይትድ ስቴትስ ሜኒሶታ ያደረገው ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ በአዲስ አበባ ከተማ ዋና ቢሮውን የከፈተው ኢትዮጵያ ሪድስ ተቋም ፣ የአሁኑ እንቅስቃሴው ሰሞነኛ ትኩረትን ሳበ እንጂ፣ ከ20 ዓመታት በላይ የህጻናትን የንባብ ክህሎት ለማሳደግ፣ የንባብ ባህልን ለማጎልበት ያለሙ ስራዎችን ሲከውን ቆይቷል ።
ኢትዮጵያ ውስጥ በሚገኙ ሰራተኞቹ ከ300 በላይ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ለሚማሩ ከ100ሺ በላይ ተማሪዎች በተለያዩ ቋንቋዎች መጽሃፍትን እንዳዳረሰ የድርጅቱ ገጽ ይናገራል ።በድርጅቱ ስሌት 1 ሚሊየን በሚሆኑ ህጻናት ዘንድ አጠቃላይ በጎ ተፈዕኖ ፈጥሯል ።
መላ ዓለም ያነጋገረው የኢትዮጵያ ውስጥ ሁኔታ ግን ፣ ድርጅቱ ወቅቱን የሚመጥን አዲስ መርሀ ግብር እንዲያሰናዳ ምክንያት እንደሆኑት ማልኮልም ክላርክ ሲያስረዱ ።
“ተቋማችን አነስተኛ ቢሆንም ህጻናት የሚያነቧቸው መጽሃፍት በማዳረስ ላይ እናተኩራለን ።የንባብ ልምድ እና ንባብን ማበረታት የሁሉም ትምህርቶች መሰረት ነው። ለዚያም ነው በዚህ ተግባር የቆየነው። በሀገሪቱ በሚገኙ በአብዛኛው የህዝብ በሆኑ ትምህርት ቤቶች ውስጥ 80 ቤተመጽሃፍን አዋቅረናል ። በአሁኑ የቀውስ ጊዜም ብዙ ተግባራት እያከናወን እንገኛለን ። የተፈናቀሉ ቤተሰቦችን በምን መልኩ ልንደግፍ እንችላለን በሚል ስናስብ ነበር ። ’’ በማለት የሀሰቡን ጥንስስ ያጋራሉ። አክለውም
“የኮቪድ 19 ቫይረስ በፈጠረው ቀውስ ምክንያት ህጻናት ቀደም ብሎ ትምህርታቸውን አቋርጠዋል። ይህ በራሱ በግለሰቦች ትምህርት ላይ ጫና ፈጥሯል ።እነዚህ ቤተሰቦች ከተፈናቀሉ በኃላ ደግሞ የተለመደ ህይወት እየገፉ አይደሉም ።ልጆች ወደ ትምህርት መሄድ አልቻሉም ። የዓለም ባንክ ሪድ አውት የሚባል መርሀ ግብር እንዳለው ከሰማን በኃላ ከባንኩ ጋር ተገናኘን። መርሀ ግብሩ ወላጆች ልጆቻቸው እንዲያነቡ ለማበረታት መጽሃፍትን ያሰራጫል ። ከእነሱ ጋር አብሮ ለመስራት ከተስማማን በኃላ ፣ በማቆያ ጣቢያዎች ውስጥ ለሚገኙ ተፈናቃይ ቤተሰቦች እና የትምህርት ዕድል ለሌላቸው ወይንም ዕድሉ ላነሰባቸው በቀጥታ መጽሃፍትን ስለማዳረስ ተወያየተናል ’’ ብለዋል ።
ተቋሙ ይሄንን ስራ የሚያከናውነው ከትምህርት ሚኒስትር እና የተፈናቀሉ ወገኖችን ጉዳይ ከሚመለከቱ ባለስልጣናት ጋረ በመተባበር ነው። የእስከአሁኑ ጥረት ከባለስልጣናትም ሆነ ለልጆቻቸው የንባብ ማስተማሪያ ቁሳቁሶችን ሲያፈላልጉ በነበሩ ወላጆች ዘንድ መልካም ምላሽ ማግኘቱን የሚናገሩት ኃላፊው ፣ በተፈናቃይ ቤተሰቦች ልክ መጽሃፍትን ለማዳረስ አለመቻላቸውን እንደ ተግዳሮት ያነሳሉ። የአሁኑ አገልግሎት የተወሰኑ ቤተሰቦች ላይ ያነጣጠረ ነው። ቀን እና አቅም ሲገጣጠም አገልግሎቱን የማስፋት አለማ እንዳላቸው ተናግረዋል ። አብረውም የሀገሬውን የንባብ ባህል የማሳደግ ህልማቸውን ያጋራሉ ።
“ ኢትዮጵያ እጅግ ድንቅ ባህል እና ታሪክ አላት ።የንባብ ባህልን በተመለከተ ግን በቤታቸው ውስጥ መጽሃፍን ለማግኘት የቻሉት እና ፍላጎት ያደረባቸው ኢትዮጵያዊያን ቁጥር ጥቂት ይመስለኛል ።በጣም ጥቂት እና በትምህርታቸው የላቁ ሰዎች እና ፈቃደኛ የሆኑ ሰዎች ብቻ ናቸው።በአንዳንዶቹ ቤተሰቦች ቤት ውስጥ ከአብዛኛው የኢትዮጵያ ቤተሰቦች የሚበልጥ የመጽሃፍ ክምችት ይገኛል ። ኢትዮጵያ ውስጥ ለንባብ የሚሆኑ ነገሮችን ማግኘት ከባድ ነው። እኒህ ህጻናት ለመደበኛ ትምህርት ምንም ዓይነት ዕድል የላቸውም ወይንም ያላቸው ዕድል አነስተኛ ነው።በእኛ በኩል መጽሃፈቱን እያዳርስን ዕውቀትን እየመገብን እንገኛለን " ብለዋል ማልኮልም ክላርክ።
የኢትዮጵያ ሪድስ የቀጣይ ጊዜያት ዕቅዶቹ ብዙ ናቸው ። ከእነዚህ መካከል አንዱ ኦፕን ሀርትስ ቢግ ድሪምስ ከተባለ ግብረሰናይ ድርጅት ጋር በመተባበር ኢትዮጵያ ውስጥ በሚነገሩ ቋንቋዎች የሚሰናዱ መጽሃፍትን የሚጽፉ ደራሲያንን ማበረታት እና ከእነሱ ጋር መስራት እንደሆነ የድርጅቱ የቦርድ ሊቀመንበር ማልኮልም ክላርክ አክለዋል።