ዛሬ ጠዋት ከ490 በላይ ኢትዮጵያውያን ወደ ሀገራቸው የተመለሱ ሲሆን፣ እስከ ቀጣዮቹ 11 ወራት ከ100 ሺህ በላይ ኢትዮጵያውያንን ለመመለስ መታቀዱን መንግሥት አስታውቋል፡፡
በሳዑዲ እስር ቤቶች ውስጥ ፈታኝ ግዜ ማሳለፋቸውን ዛሬ ከተመለሱት መካከል አስተያየታቸውን ለቪኦኤ የሰጡ ዜጎች ጠቅሰው፣ አሁንም በርካታ ኢትዮጵያውያን አስከፊ ሕይወት በመምራት ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል።
መንግሥት በችግር ላይ ላሉት አፋጣኝ ምላሽ እንዲሰጥም የጠየቁ ሲሆን፣ ዜጎችን የማስመለሱ ሥራ ያለማቋረጥ እንደሚቀጥል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ተናግረዋል።
ዛሬ ከሰዓት በኋላ ደግሞ 438 ኢትዮጵያዊያን ከሳዑዲ ወደ ሀገራቸው የተመለሱ ሲሆን፣ በአጠቃላይ ዛሬ የተመለሱት ዜጎች 936 መሆናቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።