የኢትዮጵያ መንግሥት አስቸኳይ የሰብዓዊ አቅቦቶችን ወደ ትግራይ ክልል ለማድረስ ትናንት የተናጥል የተኩስ ማቆም ማድረጉን ተከትሎ የትግራይ ክልል መንግሥት ግጭቱን በአስቸኳይ ለማቆም መወሰኑን አስታውቋል።
ተኩስ ለማቆም የተደረገው ውሳኔ የሰብዓዊ ረድኤት ድርጅቶች በሰሜን ኢትዮጵያ ለወራት ውሱን ወይም ምንም የርዳታ ተደራሽነት ላልነበራቸው በሚሊዮኖች የተቆጠሩ ተረጂዎች ምግብ፣ ውሃ እና መድሃኒት ለማቅረብ ዕድል ይሰጣቸዋል ተብሎ ይጠበቃል።
የትግራይ ክልል መንግሥት ባወጣው መግለጫ "ሕዝባችን የሚያስፈልገውን የሰብዓዊ እርዳታ መጠን እንዲደርሰው የሚያስችል ሁኔታ ተቀባይ በሆነ ጊዜ ውስጥ የሚፈጠር ከሆነ የትግራይ መንግሥት የተኩስ ማቆሙን በአስቸኳይ ተግባራዊ ያደርጋል" ያለው መግለጫ የተቁስ አቁሙ ስኬታማ እንዲሆን የቻለውን እንደሚያደርግም አስታውቋል።
የኢትዮጵያ መንግሥት ኮሚዩንኬሽን አገልግሎት ትላንት ይፋ ያደረገው የተናጥል የተኩስ ማቆም የተውሰነው ለሰብዓዊ በረራዎች ደህንነት እና የህወሓት ታጣቂዎች በሥጋት እርዳታ የሚተላልፈበትን መንገድ እንዳይዘጉ ለማድረግ መሆኑን አስታውቋል።
በከፍተኛ ችግር ውስጥ የሚገኙ ያላቸውን ዜጎች ህይወት ለመታደግ እና የዜጎችን እንግልት ለመቀነስ ይቻል ዘንድ ከተለመደው የተለዩ እርምጃዎችን መውሰድ አስፈላጊ ሆኖ መገኘቱን የጠቀሰው የኢትዮጵያ መንግሥት፣ ተኩስ ማቆም ውሳኔው ከወጣበት ሰዓት ጀምሮ ተግባራዊ የሚደረግ ለሰብዓዊነት ሲባል ግጭት የማቆም ውሳኔ ማስተላለፉን ጨምሮ ገልጿል።
የትግራይ ክልል ዛሬ ባወጣው መግለጫው የኢትዮጵያ መንግሥት የገባው ቃል ባዶ እንዳይሆን እና ያልተቆራረጠ የሰብዓዊ ርዳታ ወደ ትግራይ መግባት እንዲጀምር ተጨባጭ እርምጃዎች እንዲወስድ ጠይቋል።
ትግራይ ክልልን በመወከል የውጭ ግንኙነት የሚባል ቢሮ አስተባባሪ መሆናቸውን የሚናገሩትና በካናዳ የሚገኙት የቀድሞ የኢትዮጵያ ዲፕሎማት አቶ ዩሃንስ አብርሃ በበኩላቸው ይህንን ሐሳብ ቀደም ብለው አሳውቀው እንደነበር ተናግረዋል። የዛሬው መግለጫም የዛው ቀጣይ አካል መሆኑን ጨምረው ገልፀዋል።
ውሳኔውን ተከትሎ የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አንተኒ ብሊንከን ባስተላለፉት መልዕክት፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ለሰብዓዊነት ሲባል የተኩስ ማቆም ማድረጉንና ከሰብዓዊ እርዳታ ሰጪ ድርጅቶች ጋር በመተባበር ርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ሁሉ ያልተገደበ እርዳታ እንዲደርስ ለማድረግ መወሰኑን ዩናይትድ ስቴትስ በእጅጉ እንደምትደግፍ ተናግረዋል።
አስከትለው ማምሻውን በትዊተር ገፃቸው ላይ ባወጡት መልዕክት የኢትዮጵያ መንግሥት ያስተላለፈውን የተናጠል ተኩስ ማቆም ተከትሎ፣
"የትግራይ ክልል ባለሥልጣን በአስቸኳይ ግጭቶችን ለማቆም መወሰኑን እና ሰብዓዊ እርዳታ የለምንም ገደብ እንዲደርስ ለማድረግ አስፈላጊውን እርምጃ እንደሚወስድ አስመልክቶ ያወጣውን መግለጫ እናበረታታለን" ብለዋል።
ብሊንከን አክለው፣
"ዩናይትድ ስቴትስ ፣ሁሉም ወገኖች ትግራይን ጨምሮ አስቸኳይ እርዳታ ለሚያስፈልገው ሁሉም የኢትዮጵያ ማህበረብ ደህንነቱ በተጠበቀ እና ቀጣይነት ባለው መንገድ ድጋፍ እንዲደረግ የሚያስችለውን እርምጃ በፍጥነት እንዲወስዱ በድጋሚ ጥሪ ታቀርባለች" ብለዋል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ በበኩላቸው የተኩስ ማቆሙ በግጭቱ ውስጥ ባሉ ወገኖች ሁሉ እንዲከበር እና ሰብዓዊ እርዳታ ለሁሉም እንዲዳረስ ማንኛውም ግጭት በአስቸኳይ ለማቆም እንደሚረዳ ተስፋቸውን ገልፀዋል።
በሰሜን ኢትዮጵያ ሲካሄድ የቆየውን ግጭት በሰላማዊ መንገዶች ለመፍታት ቁርጥ አቋም እንዳለው ያመለከተው የዛሬው የትግራይ ክልል መግለጫ፣ የትግራይ ህዝብ እና መንግሥት ለሰላም እድል ለመስጠት የተቻላቸውን ሁሉ እንደሚያደርጉ አመልክቷል።
በተመሳሳይ የኢትዮጵያ መንግሥት በትናንት መግለጫው በከፍተኛ ችግር ውስጥ የሚገኙ ያላቸውን ዜጎች ችግር በአፋጣኝ የመፍታት ኃላፊነቱ ከምንም ነገርበላይ ቅድሚያ የሚሰጠው መሆኑን ጠቅሶ ዓለም ዓቀፍ ለጋሾች እያቀረቡት ያለውን ድጋፍ እና እርዳታ በከፍተኛ መጠን እንዲጨምሩም ጥሪ አቅርቧል።
ተኩስ ለማቆም የተደረገው ውሳኔ የሰብዓዊ ረድኤት ድርጅቶች በሰሜን ኢትዮጵያ ለወራት ውሱን ወይም ምንም የእርዳታ ተደራሽነት ላልነበራቸው በሚሊዮኖች የተቆጠሩ ተረጂዎች ምግብ፣ ውሃ እና መድሃኒት ለማቅረብ ዕድል ይሰጣቸዋል ተብሎ ይጠበቃል።
ለዝርዝሩ የተያያዘውን የድምፅ ፋይል ያዳምጡ።