በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የኢትዮጵያ መንግሥት ተፈናቃዮች መጠለያ ላይ የድሮን ጥቃት አርድሷል ሲል ሂዩማን ራይትስ ወች ከሰሰ


የኢትዮጵያ መንግሥት በታኅሣሥ 29/2014 ዓ.ም በሰሜን ምዕራብ ትግራይ ባካሄደው የአየር ድብደባ በሺዎች የሚቆጠሩ የትግራይ ተፈናቃዮች ተጠልለው በነበሩበት የትምህርት ቤት ግቢ ላይ ጥቃት አድርሶ ቢያንስ 57 ንፁሃን ዜጎች መገደላቸውን የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋቹ ሂዩማን ራይትስ ወች ዛሬ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

ሂዩማን ራይትስ ወች ዛሬ ከናይሮቢ ቢሮው ባወጣው መግለጫ፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ተዋጊ ሰው አልባ አውሮፕላን (ድሮን) በመጠቀም በደደቢት ከተማ በሚገኝ የትምሕርት ቤት ግቢ ላይ በጣለው ሦስት ቦምቦች 57 ንፁሃን ዜጎች ሲገደሉ 42 ደግሞ መቁሰላቸውን አስታውቋል።

የሂዩማን ራይትስ ወች የአፍሪካ ቀንድ ዳይሬክተር የሆኑት ላቲሺያ ባደር በመግለጫው ላይ እንዳመለከቱት፣ "ሦስት ግዜ የተካሄደው የድሮን ጥቃት በትምሕርት ቤቱ ህንፃ ተኝተው የነበሩ ተፈናቃይ አዛውንት፣ ሴቶች እና ህፃናትን ለሞት እና ለአካል ጉዳት ዳርጓል።" ብለዋል።

ከጥቅምት 2013 ዓ/ም ወዲህ የኢትዮጵያ ፌደራል መንግሥት ከኤርትራ እና ሌሎች አጋሮቻቸው ጋር በመሆን ከህወሃት ጋር በሚያደርጉት ውጊያ የሚያካሂደው የአየር ጥቃት እየጨመረ መሄዱን የጠቀሰው የሂዩማን ራይትስ ወች መግለጫ በደደቢት ተፈናቃዮች በተጠለሉበት አካባቢ ምንም አይነት ወታደራዊ ኢላማ የሚያሳይ ማስረጃ እንዳላገኘ ጨምሮ በመግለፅ ጥቃቱ ሆን ተብሎ የተፈፀመ ነው ብሏል።

ይህን ሂዩማን ራይትስ ወች ያወጣውን ሪፖርት በተመለከተ አስተያየታቸውን የጠየቅናቸውየኢትዮጵያ መንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዶ/ር ለገሰ ቱሉ፣ ሪፖርቱን ለጊዜው እንዳላዩት ገልፀው በሰጡት ጠቅልለ ያለ ምላሽ በሲቪል ሰዎችንላይ የተፈፀመ ጥቃት የለም ብለዋል።

የመብት ተሟጋቹ ባወጣው መግለጫ የአየር ጥቃቱ የጦር ወንጀል መባል የሚችል መሆኑን ጠቅሶ የኢትዮጵያ መንግስት ገለልተኛ ምርመራ እንዲያካሂድ ጠይቋል።

በሰሜን ኢትዮጵያ እየተካሄደ ባለው ግጭት በሁሉም አካላት የሚደርሰው የሰብዓዊ መብት ጥሰት እየተባባሰ በመሄዱም ማንኛውም የመሳሪያ ሽያጭ እና ወታደራዊ ድጋፍ ላይ ማዕቀብ እንዲጣልም መግለጫው ጨምሮ አሳስቧል።

XS
SM
MD
LG