በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ባይደን ሩሲያ ዩናይትድ ስቴትስ ላይ የሳይበር ጥቃት ልትፈጽም ትችላለች አሉ


የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳት ጆ ባይደን
የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳት ጆ ባይደን

ፕሬዚዳት ጆ ባይደን ትናንት በሰጡት መግለጫ ሩሲያ በዩናይትድ ስቴትስ ላይ የሳይበር ጥቃት ልታካሄድ ትችላለች ሲሉ አስጠነቀቁ፡፡ ሩሲያ አንድ ወር በዘለቀው የዩክሬን ወረራዋ በዩክሬን ላይ የባዮሎጂካል ወይም የኬሚካል ጦር መሳሪያዎችንም ልትጠቀም ትችላለች ብለዋል፡፡

ፕሬዚዳንት ባይደን ለዩናይትድ ስቴትስ የቢዝነስ መሪዎች ትናንት ምሽቱን ባደረጉት ንግግር የሩሲያው ፕሬዚዳንት ፑቲን እሳቸውን በመቃወም በአንድነት የተሰባሰበው ኃይል እስከዚህ ይሆናል ብለው አልጠበቁትም ሲሉ ተናግረዋል፡፡

አክለውም ማምለጫ የሌላቸው መሆኑን ለመግለጽ “አሁን ከበስተጀርባቸው ያለው ግድግዳ ብቻ ነው” ብለዋል፡፡

ይሁን እንጂ ፑቲን ለተወሰደባቸው እርምጃ አጸፋው የሳይበር ጥቃት ሊያደርጉ እንደሚችሉ ባይደን እንዲህ ሲሉ አስጠንቅቀዋል፣

“ነገር ግን ያን የማድረግ አቅሙ አላቸው፡፡ እሳካሁን አልተጠቀሙበትም፡፡ ይህ ሊያደርጉት ከሚችሉት ነገር አንዱ ነው፡፡ ይሁን እንጂ እኔ በበኩሌ፣ ሩሲያ፣ አጋሮቻችንና መላው ዓለም ለወሰደባት እርምጃ በምላሹ ጎጂ የሆነ የሳይበር ጥቃት ልታካሄድ እንደምትችል አስጠንቅቄያለሁ፡፡

ዛሬም እየወጣ ባለው የደህንነት መረጃ መሰረት፣ ሩሲያ በኛ ላይ የሳይበር ጥቃት ልታደርስ እንደምትችል በመግለጽ የኔ አስተዳደር አዲስ የማስጠንቀቂያ ትዕዛዝ አውጥቷል፡፡ ከዚህ በፊት እንደተናገርኩት የሩሲያ የሳይበር አቅም ትልቅ ጉዳት ሊያስከት የሚችል ሲሆን እየመጣ ነው፡፡ የፌዴራሉ መንግሥት በራሱ በኩል ለሚያደርገው ነገር እየተዘጋጀ ነው፡፡”

ባይደን የግሉ ከፍል የሳይበር ሴክዩክሪቲ ጥበቃና መከላከሉን እንዲያጠናክር አሳስበዋል፡፡

በዚህ ሳምንት መጨረሻ ላይ ባይደን በኔቶ ጉባኤ፣ በቡድን ሰባት እና በአውሮፓ ምክር ቤት ጉባኤ ላይ ለመካፈል በብራሰልስ እንደሚገኙ የተነገረ ሲሆን ዋናው መነጋገሪያ ዩክሬን እንደሚሆን ተመልክቷል፡፡

ባይደን ከዚያ በኋላ ወደ ፖላንድ እንደሚያቀኑም ተነግሯል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ የዩክሬን ፕሬዚዳንት ቭሎድሚር ዘለንስኪ ለአገር ውስጥ ቴሌቪዥን ትናንት በሰጡት መግለጫ ከፕሬዚዳንት ፑቲን ጋር ዩክሬን የኔቶ አባል እንደማትሆን ቃል መግባትን ጨምሮ የተኩስ አቁም ሊደረግ በሚችልበት ጉዳይ ላይ በበርካታ ጉዳዮች ለመነጋገር ዝግጁ መሆናቸውን አስታውቀዋል፡፡

XS
SM
MD
LG