የሩሲያ ወታደራዊ ባለሥልጣናት ዛሬ ቅዳሜ በሰጡት መግለጫ በዩክሬን ለመጀመሪያ ጊዜ ሃይፐርሶኒክ የተባሉ (ከድምጽ የፈጠኑ) ሚሳዬሎችን መተኮሳቸውን አስታወቁ፡፡
የሩሲያ መከላከያ ሚኒስቴር በመግለጫው “ኪንዝሃል የተባለውን እጅግ ፈጣን የሆነ፣ የሃይፐር ሶኒክ ባለስቲክ ሚሳዬል፣ በዩክሬን ምዕራባዊ ክፍል፣ ኢቫኖ ፍራንክፊዝክ ግዛት፣ ዴሊያትን ውስጥ በሚገኝ ግዙፍ፣ የምድር ውስጥ የጦር መሳሪያ ማካመቻን በመደብደብ፣ በውስጡ የነበሩትን ሚሳኤሎችና የአየር መገናኛ መሳሪያዎችን አውድሟል” ብሏል፡፡
ጥቃቱ የተፈጸመው ትንናት ዓርብ የነበረ ቢሆንም የሩሲያ መከላከያ ሚኒስቴር መግለጫን ትክክለኝነት ለማረጋገጥ አልተቻለም፡፡
የዩክሬን ባለሥልጣናት ባወጡት መግለጫ የሩሲያ የኪንዝሃል ሚሳዬልን መጠቀምና ያለ አንዳችች ምህረት የሰላማዊ ዜጎችን በጅምላ በቦምብ መደብደብ፣ በጦር ሜዳው ስልትና ግቦች እንዲሁም በእግረኛ ተዋጊዎቻቸውም ምን ያህል ያልተሳካላቸው መሆኑን ይገልጻል ብለዋል፡፡
የዩክሬን ጦር ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ጄነራል፣ ዛሬ ቅዳሜ በሰጡቱ መግለጫ ሩሲያ ባለፉት 24 ሰዓታት ውስጥ ብቻ በመላው ዩክሬን ወደ 14 ሚሳዬሎችን መተክሷን፣ 40 የአየር ድብደባዎችን ማድረጓንና በዋነኝነት ሰላማዊ ዜጎችን ማጥቃቷን አስታውቀዋል፡፡
ሩስያ ወታደሮቿ ደቡባዊ ዩክሬን ወደምትገኘው ማሪዮፑል የወደብ ከተማ መዝለቃቸውን መግለጿን የዩክሬን ባለሥልጣናት አምነዋል፡፡
ለቀናት ስትደበደብ በቆየችው በዚህ ከተማ 300ሺ የሚደርሱ ነዋሪዋችዋ ምግብ ውሃ መብራትና ኢንተርኔት አጥተው የሰዎችም አስክሬን በየጎዳናውና በረንዳው ላይ መዘርጋቱን ገልጸዋል፡፡
የዩክሬን ፕሬዚዳንት ቮሎድሚር ዘለንስኪም “ዛሬ ቅዳሜ ከተማዪቱ በዩክሬን ታሪክ ታይቶ የማያውቅ ትልቅ መከራ እየተቀበለች ነው ሲሉ” ተናግረዋል፡፡