የዩናይትድ ስቴትስ ምክትል ፕሬዚዳንት ካማላ ሃሪስ ባለቤት ደግ ኢምሆፍ ኮሮናቫይረስ እንደያዛቸው በምርመራ መታወቁን ዋይት ኃውስ አስታወቀ። ባለቤታቸው ምክትል ፕሬዚዳንት ሃሪስ ተመርምረው ከቫይረሱ ነጻ ሲሆኑ ሆኖም በባለቤታቸው መጋለጥ የተነሳ የሥራ መርኃ ግብሮቻቸውን ቀንሰዋል።
ሃሪስ በትዊተር ባወጡት ቃል "ደግ ደህና ነው፥ ክትባቶቻችንን ከነማጠናከሪያው መውሰዳችን ጥሩ ነው" ብለዋል።
ምክትል ፕሬዚዳንቷ ትናንት ማታ በዋይት ኃውስ በተካሄደው የእኩል ክፍያ ጉዳይን የተመለከተ ዝግጅት ላይ አልተገኙም ሆኖም ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን እንዲህ ብለዋል።
"በቡድናችን እኮራለሁ። በተለይም ደግሞ ዛሬ በዚህ ዝግጅት ሊያቀርቡኝ በነበሩት በካማላ ሃሪስ እኮራለሁ። ባለቤታቸው ለቫይረሱ መጋለጣቸውን ተከትሎ ምንም እንኳን እንደተነገረኝ ባለቤታቸው በጣም ጥሩ የጤና ሁኔታ ላይ ቢሆኑም ለጥንቃቄ ሲሉ አለመምጣቱን መርጠዋል፣ ለጥንቃቄ ሲሉ ነው ያልመጡት” ብለዋል።
ምክትል ፕሬዚዳንት ሃሪስ ትናንት ከሰዓት በኋላ ከፕሬዚዳንት ባይደን ጋር የነበሩ ሲሆን የአንድ ነጥብ አምስት ትሪሊዮን ዶላር የመንግሥት በጀት በተፈረመበት ስነ ስርዐት ላይ ከምክር ቤት አባላት ጋር ተገናኝተዋል።