ዩክሬን የተደረሰበትን የተኩስ አቁም ስምምነት በመጣስ ጦርነቱን በመሸሽ በሚወጡ ሰላማዊ ዜጎች መውጫ ኮሪደር ላይ የሩሲያ ኃይሎች እየተኮሱ ነው ስትል ዛሬ ከሳለች፡፡
የሩሲያ መከላከያ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ስምምነቱ ከተደረሰባቸው የማሪፖል እና ቮልኖካቫ ለቀው ለሚወጡ የሰላማዊ ዜጎች በሞስኮ አቆጣጠር ከማለዳው አንድ ሰዓት ጀምሮ መውጫው መንገድ ክፍት የሚደረገና ተኩስ የሚቆም መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የማሪዩፖል ባለሥልጣናት ግን ነዋሪዎቹ ከተማውን ለቀው የሚወጡበትን ጊዜ በማዘግየት ይልቁንም ራሳቸውን ወደሚያድኑበት መጠለያ እንዲገቡ አሳስበዋል፡፡
ሰላማዊ ዜጎቹ እንዲወጡ ለአምስት ሰዓታት የሚቆይ የአውቶብስና የግል ተሽከርካሪዎች መስመር ክፍት እንዲደረግ ታቅዶ እንደነበርም ተገልጿል፡፡
በተያያዘ ዜናም የዩናትድ ስቴትስ መከካለያ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ የሩሲያ ኃይሎች በትናንትናው እለት በኦዴሳ አቅራቢያ ያለውን የዩክሬናውያን ከተማ እየደበደቡ መሆኑን አስታውቋል፡፡
በኪየቭ አቅራቢያ ያለው የሩሲያ እግረኛ ጦርም እስካሁን ወደ ከተማው ለመጠጋት እየሞከረ መሆኑን ሲገልጽ በዩክሬናውያኑ ብርታት ግስጋሴው መገታቱ ተመልክቷል፡፡