የዩክሬን ባለስልጣናት የሩሲያ ኃይሎች በዩክሬን የሚገኘውን የአውሮፓ ግዙፉን የኒውክሌር ማብላያ እንደተቆጣጠሩ አስታወቁ፡፡ ባለስልጣናቱ በዩክሬን አነርሆዳር በሚገኘው የዜበርዚያ ማብላያን ከከፍተኛ የአየር ጥቃት በኋላ መቆጣጠራቸውን አስታውቀዋል፡፡
የዩክሬን ኒውክለር ማብላያው ተቆጣጣሪ እስካሁን ድረስ ከማብላያው ምንም ዓይነት የጨረር ፍሰት አለመኖሩን ገልጸው ሃላፊዎቹ በቦታው በሰላማዊ መንገድ ስራቸውን እየሰሩ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ የዩክሬን ባለስልጣናት የእሳት አደጋ ሰዎች በአካባቢው የተነሳውን እሳት በቁጥጥር ስር ማዋላቸውንም ገልጸዋል፡፡
ኤነርሆዳር ከዋና ከተማዋ ኪየቭ በደቡባዊ ምስራቅ አቅጣጫ በ700 ኪ.ሜ ርቀት ላይ የምትገኘው ዲኒፐር ወንዝ አካባቢ ላለ ከተማ የሃይል ምንጭነት የሚያገለግል ሲሆን ማዕከሉ 25 በመቶ የሚሆነው የአጠቃላይ ዩክሬን የሃይል ምንጭ ነው፡፡
የዩናይትድ ስቴትሱ ፕሬዘዳንት ጆ ባይደን የዩክሬኑ ፕሬዘዳንት ቮለዲመር ዚለንስኪ በጉዳዩ ላይ እንዳነጋገሩ ትላንት ማምሻውን ከዋይት ሃውስ የወጣ መግለጫ አስታውቋል፡፡
የፕሬዘዳንት አስተዳደር ለዩክሬን እና ለጎረቤት ሃገራት ለሚደረግ ተጨማሪ የሰብዓዊ፣ የደህንነት እና የምጣኔ ሃብት ድጋፍ የሚውል የ10 ቢሊየን ዶላር ድጋፍ ኮንግረሱን ጠይቋል ሲሉ የበጀት አስተዳደር ቢሮ ዳይሬክተር ሻላንዳ ያንግ አስታውቀዋል፡፡ ሃላፊዋ ጥብቅ የሆነ ማዕቀብ፣ የወታደሮች ስምሪት፣ የመከላከያ መሳሪያ ድጋፍ እና የአስቸኳይ ምግብ ድጋፍ ወደ ጎረቤት ሃገራቱ ይላካሉ ብለዋል፡፡
በተያያዘ ዋሺንግተን ከብላድሚር ፑቲን ጋር ቁልፍ ግንኙነት አላቸው በተባሉ ሰዎች ላይ ተጨማሪ ማዕቀቦችን ጥላለች፡፡
ባይደን ትላንት ከካቢኔያቸው ጋር በነበራቸው ውይይት “ዛሬ ከ10 በላይ የሚሆኑ ቀንደኛ የሩሲያ ቢሊየነሮችን ጨምሮ 50 የሚደርሱ ከበርቴዎችን፣ ቤተሰቦቻቸውን እና ባልደረቦቻቸውን ወደ አሜሪካ እንዳይገቡ የጉዞ ክልከላ ማድረጌን አስታውቃለሁ” ያሉ ሲሆን “በተመሳሳይ ለዩክሬን ሕዝቦች በቀጥታ ድጋፍ ማድረጋችንን እንቀጥላለን” ብለዋል፡፡
ማዕቀቡ የፑቲን የቅርብ አጋር እና የሩሲያ ከፍተኛ ባለሃብት የሆኑትን ኦሊቨር ኡስማኖቭ እና የሩሲያ ቅጥር ወታደሮችን የሚመራው የዋግር ግሩፕ ሃላፊ እና የፕሬዘዳንት ፑቲን ቃል አቀባይ ዲሚትሪ ፔስኮቭንም ያካተተ ነው፡፡
በሌላ በኩል የሩሲያ ወታደሮች የውደብ ከተማ የሆነችው የምስራቃዊ ካህርሰን ከተማ ማሪፖልን በመክበብ ዩክሬንን ከሌላው ዓለም ለማቆራረጥ እየሞከሩ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡