በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በፓኪስታን መስጊድ ውስጥ በአጥፍቶ ጠፊዎች በደረሰ የቦንብ ጥቃት የ56 ሰዎች ሕይወት አለፈ 


በፓኪስታን፣ ፔሻዌር የእርዳታ ሰራተኞች እና በጎ ፍቀደኞች የቦንብ ጥቃቱ በደረሰበት ስፍራ ተሰብስበው -  March 4, 2022.
በፓኪስታን፣ ፔሻዌር የእርዳታ ሰራተኞች እና በጎ ፍቀደኞች የቦንብ ጥቃቱ በደረሰበት ስፍራ ተሰብስበው -  March 4, 2022.

በሰሜን ምዕራብ ፓኪስታን በሚገኝ አንድ የሻዓ ሙስሊሞች መስጊድ በደረሰ የቦንብ አደጋ 56 ሰዎች ሲሞቱ ሌሎች 194 ሰዎች ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡ ይህ አስከፊ የሆነ ጥቃት በሃገሪቱ አናሳ በሆኑት የሸዓ ተከታዮች ላይ የደረሰው ምዕመናኑ ለአርብ ሰላት በሃገሪቱ ሰሜን ምዕራብ ክፍል ከይበር ፓክቱንካህዋ በተሰኘው ግዛት ዋና ከተማ በማዕከላዊ ፔሻዌር በተጨናነቀ ሁኔታ በተሰባሰቡበት ነው፡፡

በአቅራቢያው የሚገኘው የሌዲ ሬዲ ሆስፒታል ቃል አቀባይ ሞሃመድ አሲም የደረሰውን ጉዳት ያረጋገጡ ሲሆን ጉዳት ከደረሰባቸው ውስጥ 12 የሚሆኑ ሰዎች ለሕይወታቸው አስጊ በሆነ ሁኔታ እንደሚገኝ ተናግረዋል።


የሃገሪቱ ከፍተኛ የፖሊስ ሃላፊ ሃሩን ራሺድ ለጋዜጠኞች ሁኔታውን ያስረዱ ሲሆን ጥቃት አድራሾቹ ቃሳ ካዋኒ በተሰኘው ባዛር ወደ ሚገኘው መስጊድ በማምራት በበሩ ላይ ቆመው የነበሩ ሁለት ፖሊሶችን በመግደል እንደገቡና በመቶዎች የሚቆጠሩ ምዕመናን በተሰባሰቡበት የታጠቁትን ቦንብ ማፈንዳታቸውን ገልጸዋል፡፡

የሃገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ኢምራን ካህን ጥቃቱን ያወገዙ ሲሆን ጉዳት ለደረሰባቸው ሰዎች አስቸኳይ ድጋፍ እንዲደረግ ባለስልጣናቱን ማዘዛቸውን ቢሯቸው አስታውቋል፡፡ በፓኪስታን ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ለሚፈጸሙ የቦንብ ጥቃቶች ማንም ሃላፊነት እየወሰደ አይደለም፡፡

በዋናንነት የሱኒ ሙስሊሞች በሚበዙበት ፓኪስታን በሸዓ ሙስሊሞች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶች የተለመዱ ሲሆኑ ከዚህ ቀደም ተመሳሳይ ጥቃቶች በታሊባን እና እራሱን እስላማዊ መንግስት ብሎ በሚጠራው የሽብር ቡድን ተፈጽመዋል፡፡

በኢስላማባድ የሚገኘው የዩናይትድ ስቴትስ ኤማባሲ በፔሻዌር መስጊድ ላይ የተፈጸመውን ዓይነት አስከፊ እና የፈሪ ጥቃትን እናወግዛለን ያሉ ሲሆን ለተጠቂዎቹ እና ለቤተሰቦቻቸው ሃዘናችንን እናስታውቃለን በማለት በትዊተር ገጻቸው ላይ አስታውቀዋል፡፡

የዛሬው ጥቃት ከሃያ አራት አመታት በኋላ ለመጅመሪያ ጊዜ በፓኪስታን በክሪኬት ስፖርት ላይ ለመሳተፍ የአውስትሬሊያ የስፖርት ቡድኖች ወደ ሃገሪቱ ከገቡ በኋላ የተፈጸመ ሲሆን የሁለቱ ሃገራት ቡድኖች በርዋንዲፒ በአስጨናቂ ሁኔታ በመሆን ግጥሚያ አድርገዋል፡፡

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በፓኪስታን በተደጋጋሚ በሚደርሱ ጥቃቶች ሳቢያ በክሪኬት ስፖርት የሚታወቁ ሃገራት ቡድኖቻቸውን ወደሃገሪቱ መላክ አቁመዋል፡፡

XS
SM
MD
LG