በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ አረፉ     


ከኢትዮጵያ አርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርሰቲያን መገናኛ ብዙኀን አገልግሎት የተገኘ ምስል፡፡
ከኢትዮጵያ አርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርሰቲያን መገናኛ ብዙኀን አገልግሎት የተገኘ ምስል፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋኅዶ ቤተ ክርስቲያን አራተኛ ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ማረፋቸውን የቅዱስ ሲኖዶስ ፅህፈት ቤት አስታውቋል።

ቅዱስነታቸው ህክምና ላይ እንደነበሩም ተገልጿል።

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ኢህአዴግ ወደ መንበረ ሥልጣን በወጣባቸው የመጀመሪያ ዓመታት ሃገራቸውን ጥለው ከወጡ በኋላ ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ የኖሩ ሲሆን በስደት ተቋቁሞ በ2010 ዓ.ም. መጨረሻ አካባቢ ተመልሶ ሃገር ቤት ካለው ቅዱስ ሲኖዶስ ጋር እስከተዋሃደበት ጊዜ የቆየውን “ስደተኛው” እየተባለ ሲጠራ የነበረውን ሲኖዶስ ሲመሩና በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ-ኢትዮጵያዊያን ሲያገለግሉ ቆይተዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ አስተዳደር ሥልጣን ሲረከብ የተደረገን ብርቱና ተከታታይ ሽምግልና ተከትሎ በሀገር ቤት ከነበረው ሲኖዶስ ጋር እርቅ በመውረዱ ቅዱስነታቸው በሃምሌ 2010 ዓ.ም. ወደ ሀገራቸው ተመልሰው አሁን ካሉት ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ጋር በመንፈሳዊ መሪነት መንበረ ፓትርያኩ ላይ ቆይተዋል።

ባለፉት ወራት የጤናቸው ሁኔታ ተስተጓጉሎ መቆየቱ የተነገረው አቡነ መርቆሬዎስ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ህመሙ ጠንቶባቸው እንደነበረ ተገልጿል።

ፕሬዚደንት ሳህለወርቅ ዘውዴና ሌሎችም የመንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣኖች፣ እንዲሁም የሩስያና የአሜሪካ ኤምባሲዎች ለቅዱስ ሲኖዶሱ የኀዘን መልዕክት አስተላልፈዋል።

የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ አስከሬን ሥርዓተ-ሽኝት ከነገ በስተያ ዕሁድ፤ የካቲት 27 ቀን 2014 ዓ.ም በመንበረ-ፀባዖት ቅድስት ሥላሴ ቤተክርስትያን እንዲከናወን የኢትዮጵያኦርቶዶክስ ተዋኅዶ ቤተክርሰትያን ቅዱስ ሲኖዶስ ዛሬ ባካሄደው አስቸኳይ ጉባዔ መወሰኑን የቤተ-ክህነቷ መገናኛ ብዙኃን ድርጅት ዘግቧል።

XS
SM
MD
LG