በርካታ መንግሥታት በሚዲያ ላይ ጠበቅ ያለ ቁጥጥር በሚያደርጉባት ምዕራብ አፍሪካ ውስጥ የሚዲያ ነፃነት መዲና ተደርጋ በምትቆጠረው ጋና፣ በቅርቡ ቁጥሩ እየጨመረ የመጣው የጋዜጠኞች እስርና እንግልት አሳሳቢ መሆኑ ተገለፀ።
ከወር በፊት ሁለት ጋዜጠኞች፣ የሀገሪቱ ቀዳማዊት እመቤት የመንግሥትን መሬት ወስደው የግል ቤታቸውን ሰርተውበታል በማለታቸው ለእስር የተዳረጉ ሲሆን፣ አንድ ሌላ ጋዜጠኛ ፕሬዚዳንቱ በምርጫ አቤቱታዎች ዙሪያ የዳኞች ውሳኔ ላይ ተፅእኖ ያደርጋሉ ብሎ በመክሰሱ መታሰሩ ተዘግቧል።
ሦስቱም ጋዜጠኞች ክስ የተመሰረተባቸው ሀሰተኛ ወሬን በማሰራጨት ሲሆን፣ ጥፋተኛ ሆነው ከተገኙ ረጅም እስር ይጠብቃቸዋል።
የመንግሥትቃል አቀባይ የሆኑት ፓልግሬቭ ቦካዬ ዳንቃ በበኩላቸው፣ የመናገር ነፃነትን እንደማያፍን፣ ሆኖም ባለሥልጣናት ሚዲያው የመናገር ነፃነትን ያለአግባብ እየተጠቀሙበት መሆኑ እንደሚያሳስባቸው ገልፀው፣ የታሰሩት ጋዜጠኞች ፕሬዚዳንቱን እና ባለቤታቸውን ያለማስረጃ መጥፎ ተግባር እንደፈፀሙ አድርገው መክሰሳቸውን ተናግረዋል።