የየመን ሁቲ አማጺያን በሳውዲ አረቢያ የሚገኝ አውሮፕላን ጣቢያን ለማጥቃት የተላከን ድሮን በሳውዲ የሚመራው የጦር ቅንጅት ለማውደም ቢችልም 16 የውጭ ሀገራት ዜጎች ግን ጉዳት እንደደረሰባቸው ተሰምቷል። በሁለት ሳምንታት ውስጥ ሁለተኛው ለሆነው ለዚሁ ጥቃት ኃላፊነቱን የወሰዱት በኢራን የሚደገፉት ሁቲ የየመን አማጺያን ናቸው።
አማጺያኑ መግፋታቸውን ተከትሎ፣ ላለፉት 7 ዓመታት ያህል የየመንን መንግሥት ለመደገፍ የተቀናጀውን ጦር በመምራት ላይ በምትገኘው ሳውዲ አረቢያ ላይ ጥቃቶችን ተከታትለዋል።
የጦር ቅንጅቱ ለሳውዲ ዜና አገልግሎት እንዳስታወቀው ጄዛን ወደሚገኘው ወደ ንጉሥ አብዱላህ አውሮፕላን ማረፊያ የተለካው ድሮን አየር ላይ እንዲወድም ከተደረገ በኋላ ፍንጥርጣሪዎቹ አውሮፕላን ማረፊው ግቢ ወድቀዋል።
በየመን ሰንዓ የሚገኘው የአውሮፕላን ማረፊያ፣ በአውሮጳዊያኑ የካቲት 10 በሳውዲ ደቡብ ምዕራብ ቀጠና ለደረሰው ጥቃትም ኃላፊነቱን በወሰዱት ሁቲ አማጺያን እጅ ይገኛል።
የአብሃን ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ጣቢያ ኢላማ ባደረገው በዚያ ጥቃት፣ 12 ሰዎች ተጎድተዋል። በአጻፋው ሳውዲ መሩ የጦር ቅንጅት ለድሮን ጥቃቱ የዋለ ሰንዓ ውስጥ ከሚገኘው የቴሌኮም ሚኒስቴር አቅራቢያ የሚገኝ የግንኙነት ሥርዓትን ማውደሙን አስታውቋል።
በታህሳስ ወር ቅንጅቱ፣ ባለፉት ሰባት ዓመታት የሁቲ አማጺያን 850 ጊዜ የድሮን፣ 400 ጊዜ የባለስቲክ ሚሳኤል ጥቃት በሳውዲ አረቢያ ላይ በመክፈት 59 ሰዎችን ገድለዋል ሲል አስታውቋል፤ ዘገባው የኤፍፒ ነው።