በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በየመኗ የነዳጅ ማከማቻ መርከብ ጉዳይ ሥምምነት መደረሱን ተመድ አስታወቀ


የሳተላይት ምስል ኤፍኤስኦ ሴፈር ዘይት ጫኝ በየመን ራስ ኢሳ የባህር ተርሚናል ላይ ያለውን እይታ ያሳያል።
የሳተላይት ምስል ኤፍኤስኦ ሴፈር ዘይት ጫኝ በየመን ራስ ኢሳ የባህር ተርሚናል ላይ ያለውን እይታ ያሳያል።

በአካባቢው ከፍተኛ ብክለት እንዳይደርስ ሥጋት ደቅና ከየመን የባህር ጠረፍ ጥገና ሳይደረግላት ለረዥም ጊዜ ከቆመችው FSO Safer ከተባለች የነዳጅ ማከማቻ መርከብ ላይ የሚገኘውን ድፍድፍ የነዳጅ ዘይት ወደ ሌላ ለማዘዋወር ለያዘው እቅድ በመርህ ደረጃ ከሥምምነት መድረሱን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አስታወቀ።

የመንግስታቱ ድርጅት የሰብአዊ ጉዳዮች ኃላፊ ማርቲን ግሪፊዝ ናቸው ትላንት ለፀጥታው ምክር ቤት አስተያየት በሰጡበት ወቅት የተደረሰውን ስምምነት ይፋ ያደረጉት።

ግሪፊዝስ የሥምምነቱን ዝርዝርም ሆነ የተባለውን ነዳጅ ከመርከቢቱ የማራገፉ እና ወደ ሌላ የማስተላለፉ ሥራ መቼ እንደሚጀመር አልተናገሩም።

የየመን ብሔራዊ የነዳጅ ኩባንያ ንብረት የሆነችው FSO Safer እንደ አውሮፓውያን የዘመን አቆጣጠር ከ1980ዎቹ መጨረሻ አንስቶ በየመኗ የሆዴይዳ ግዛት ከሚገኝ የባህር ጠረፍ ዘጠኝ ኪሎ ሜትሮች ርቀት ላይ በነዳጅ ዘይት ማከማቻነት ስታገለግል የቆየች ናት።

መርከቢቱ መጠኑ አንድ ነጥብ አንድ ሚሊዮን በርሜል የሚሆን ድፍድፍ የነዳጅ ዘይት ተሸክማለች። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ግን እንደ አውሮፓውያን የዘመን አቆጣጠር ከ2015 ዓም አንስቶ “ያለችበት ሁኔታ አልተመረመረም ወይም በአግባቡ አልተጠበቀም” ይላል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣናት በበኩላቸው ከመርከቢቱ ጭነት የሚፈስ የነዳጅ ዘይት ለየመን የሚላክ ምግብ እና የሰብአዊ እርዳታ ወሳኝ መተላለፊያ የሆነው የሆዴዳ ወደብ እንዲዘጋ እንዳያስገድድ ስጋት አለን” ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

የነዳጅ መፍሰስ አደጋ ከደረሰ በዓሣ ማጥመጃ ስፍራዎች ላይ ብክለት ሊያስከትል፣ በቀይ ባህር የሚተላለፉ የንግድ ማጓጓዣ መርከቦችን መተላለፊያ ሊዘጋ እና ብሎም በአካባቢው ባሉ ሌሎች አገሮች ላይ ጉዳት ሊያደርስ ይችላል የሚል ሥጋት መኖሩም ይታወቃል።

XS
SM
MD
LG