በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በናቫልኒ ላይ የቀረቡት ክሶች አጠራጣሪ ናቸው ስትል ዩናይትድ ስቴትስ ክሬምሊንን ወቀሰች


የዩናይትድ ስቴትሱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንተኒ ብሊንከን
የዩናይትድ ስቴትሱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንተኒ ብሊንከን

በተቃዋሚ መሪ አሌክሲ ናቫልኒ ላይ ሩስያ ያቀረበችው “አጠራጣሪ አዳዲስ ክሶች ረብሸውኛል” ሲሉ የዩናይትድ ስቴትሱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንተኒ ብሊንከን ተናገሩ።

ትናንት ማክሰኞ ከሞስኮ ወጣ ብሎ በሚገኝ እና እስረኞችን ለማሰቃየት ይጠቀሙበታል ከሚባለው የፍርድ ሂደታቸው እየታየ ካለበበት ሥፍራ የተሰሙት አዲሶቹ ክሶች ናቫልኒ ገንዘብ በማጭበርበር እና ፍርድ ቤትን በመናቅ የሚሉ ጥፋተኛ ሆነው ከተገኙም እስከ 15 ዓመት እስራት ሊያስቀጧቸው የሚችሉ ናቸው።

"ናቫልኒ እና አጋሮቻቸው በባለ ሥልጣናት የሚፈጸሙ የሙስና ድርጊቶችን በማጋለጣቸው ነው ዒላማ የተደረጉት" ሲሉ በትዊተር ገጻቸው ያሰፈሩት ብሊንከን፣ “የሩሲያ ባለሥልጣናት ናቫልኒን ከእስር እንዲለቁ እና በደጋፊዎቻቸው ላይ የሚፈጽሙትን ወከባ እና ውንጀላም እንዲያቆሙ” ያሉበትን ጥሪ አሰምተዋል።

ክሬምሊን ላይ ጠንካራ ትችት በማቅረብ የሚታወቁት ናቫሊ እንደ አውሮፓውያን የዘመን አቆጣጠር ጥር 2021 ተይዘው የታሰሩት በተቃጣባቸው የመርዝ ጥቃት በጀርመን በማገገም ላይ ሳሉ ቀደም ሲል “በይቅርታ ሲለቀቁ የተጣለባቸውን ገደብ ተላልፈው ለበርካታ ወራት ቆይተዋል” በሚል ነው። ለዚያም የሁለት ዓመት ተኩል እስራት ተፈርዶባቸው ቅጣታቸውን በመወጣት ላይ ነበሩ።

የሩስያ መርማሪዎች በእስር ላይ ሳሉ ያቀረቡባቸው አዲሱ ክስ ደግሞ፣ ናቫሊ በእንግሊዝኛው ምህጻረ ቃል FBK በመባል ለሚታወቀው የጸረ ሙስና ድርጅታቸው የተለገሰ ገንዘብ “ዘርፈዋል” የሚል ሲሆን፤ ችሎት መዳፈር የሚለው ሌላው ክስ ደግሞ ናቫሊ ካሁን በፊት ክሳቸው በመታየት ላይ በነበረበት ወቅት ዳኛውን ዘልፈዋል” የሚል ነው።

"ይህ የፍርድ ሂደት እንዲካሄድ ያዘዙት እነዚህ ሰዎች በእውነት ፈርተዋል" ሲሉ በችሎቱ ወቅት የተናገሩት የ45 ዓመቱ ናቫልኒ "በዚህ ችሎት ወቅት ስለምናገረው እና ክሱም በሃሰት የተቀነባበረ መሆኑን ሕዝብ በግልፅ የሚያየው መሆኑ ስጋት አሳድሮባቸዋል።" ነው ያሉት።

“የፖለቲካ ዓላማ ለማስፈጸም የተጠነሰሰ” ሲሉም ክሱን ሙሉ በሙሉ አስተባብለዋል።

ናቫልኒ አክለውም "ይህን ፍርድ ቤት፣ ይህን የቅጣት ስፍራ፣ ወይም የፌድራሉን የደህንነት መሥሪያ ቤት፣ አቃብያነ ህጉን፣ የኬሚካል ጦር መሳሪያዎቹን፣ ፑቲንንም ሆነ ሌሎቹን፣ አንዳቸውንም አልፈራም" ሲሉ ለፍርድ ቤቱ መናገራቸውን በቪዲዮ ተቀርጾ የተሰራጨው መግለጫ ያሳያል።

"አልፈራም። ምክንያቱም ይህን መፍራት ውርደት እና ረብ-የለሽ መሆኑን ስለማምን።" ነበር ያሉት።

አጋሮቻቸው ውንጀላውን ሲያወግዙ፣ ጠበቃቸው በበኩላቸው ክሬምሊን ደምበኛቸውን ዝም ለማሰኘት ያውጠነጠነው ሙከራ ነው፣ ብለዋል።

XS
SM
MD
LG