ራሽያ ዩክሬንን ልትወር ትችላለች የሚለው ስጋት እያየለ መሄዱን ተከትሎ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን እና የራሽያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ዛሬ የስልክ ውይይት ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ዋሽንግተን ራሽያ ምናልባት ረቡዕ ወረራውን ልትፈፅም ትችላለች የሚል የደህንነት መረጃ የደረሳት ሲሆን በኪየቭ የሚገኘው የዩናይትድ ስቴትስ ኤምባሲ ሰራተኞቹን ማስወጣት መጀመሩ ታውቋል። የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው የጉዞ ማስጠንቀቂያም 'የራሽያ ሰራዊት እርምጃ ሊወስድ ይችላል የሚለው ፍራቻ እያየለ መምጣቱን ተከትሎ' ሰዎች ወደ ዩክሬን እንዳይጓዙና፣ በውስጥም ያሉት በአቸኳይ እንዲወጡ አዟል።
እንግሊዝ፣ ጀርመንና ኔዘርላንድም በተመሳሳይ ዜጎቻቸው በአስቸኳይ ከዩክሬን እንዲወጡ እያሳሰቡ መሆናቸውም ተገልጿል።
የራሽያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ማሪያ ዛካሮቫ በበኩላቸው ከኪየቭ በኩል የሚነሳው ትንኮሳ እያየለ በመምጣቱ ሞስኮ በዩክሬን ያላትን ዲፕሎማቶች ቁጥር መቀነሳቸውን ተናግረዋል። ዛካሮቫ የራሽያን እርምጃ በዝርዝር ባያስረዱም በዩክሬን የሚገኘው የራሽያ ኤምባሲ እና ሰራተኞች ቁልፍ ጉዳዮች ላይ ስራቸውን እንደሚቀጥሉ ግን ተናግረዋል።
ባይደን እና ፑቲን የስልክ ውይይቱን ከማድረጋቸው በፊት ፑቲን በዚህ ሳምንት መጀመሪያ አግኝተዋቸው ከነበሩት የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማርኮን ጋር እንደሚነጋገሩም ተገልጿል።
የዋይት ኃውስ ብሄራዊ ደህንነት አማካሪ ጄክ ሱሊቫን አርብ እለት ሲናገሩ የኦሎምፒክ ውድድር በሚካሄድበት ወቅት ራሽያ ዩክሬንን ልትወር ትችላለች ብለው የነበረ ሲሆን በርካታ ተንታኞች ግን በቻይና የሚካሄደው የክረምት ኦሎምፒክስ ሳይጠናቀቅ ራሽያ ምንም አይነት እርምጃ ላትወስድ ትችላለች ብለው ያምናሉ።
ሱሊቫን ራሽያ በአሁኑ ወቅት ማንኛውንም ርምጃ መውሰድ የሚያስችላት ወታደራዊ ሀይል በዩክሬን ድምበር ላይ ማከማቸቷን የገለፁ ሲሆን ዋና ከተማዋን ኪየቭን ጨምሮ ከፍተኛ መጠን ያለውን የዩክሬን ግዛት ለመቆጣጠር ትችላላእች ብለዋል።
አንድ የዩናይትድ ስቴትስ መከላከያ ሚኒስቴር ባለስልጣን ለጋዜጠኞች ሲናገሩ ባይደን በፖላንድ ከነበራቸው 1ሺህ ሰባት መቶ ወታደሮች ተጨማሪ 3ሺህ ወታደሮች ለመላክ መወሰናቸውን ገልዋል። ወታደሮቹ የሚላኩት ለሰሜን ጦር ቃልኪዳን ድርጅት (ኔቶ) አባላት የደህነት ማረጋገጫ ለመስጠትና በምስራቅ ክንፍ የሚገኙ የኔቶ አባላት ላይ ጥቃት እንዳይሰነዘር ለመከላከል መሆኑም ተጠቁሟል።