ዋሽንግተን ዲሲ —
የቱኒዝያ ፕሬዚዳንት ካዪስ ሰዒድ የሃገራቸውን ጠቅላይ የዳኝነት ምክር ቤት ዛሬ መበተናቸውን አስታውቀዋል።
ፕሬዚዳንቱ እርምጃውን የወሰዱት የሃገሪቱ ከፍተኛው የፍትኅ አካል በተለይ የሙስናና የሽብር ፈጠራ ክሦችን በያዙ ዶሴዎች ላይ ዘገምተኛ እንደሆነ በመግለፅ ትችትና ወቀሳ ለወራት ሲያሰሙ ከቆዩ በኋላ መሆኑን ሮይተርስ ዘግቧል።
“ዳኞች የመንግሥቱ ተግባራት አካል ናቸው እንጂ በራሳቸው እንደመንግሥት እንዲንቀሳቀሱ አልፈቅድም” ሲሉም ፕሬዚዳንቱ ክሥ አዘል መልዕክት ሲያሰሙ ቆይተዋል።
የፕሬዚዳንት ካዪስ ሰዒድ የዛሬ እርምጃ የፍርድ ቤቶችን ነፃነት እንዳይጋፋ ሥጋት እንዳሳደረባቸው የሚገልፁ ተቀናቃኞቻቸውን የበረታ ተቃውሞ ሳያስነሳባቸው እንደማይቀር እየተሰማ ነው።