ቻይና በቅርቡ ከአፍሪካ ጋር የተፈራረመችው የበርካታ ቢሊየን ዶላር ስምምነት ቻይና፣ የውጪ ንግድ፣ የዲጂታል ፈጠራ፣ ህክምና፣ ድህነትን መቀነስ፣ ባህል እና ሰላም እና ፀጥታን ጨምሮ፣ በተለያዩ ዘጠኝ የኢንዱስትሪ ዘርፎች አፍሪካ ላይ ተጨማሪ ገንዘብ ለማፍሰስ የወሰደችው ትልቅ ርምጃ ነው።
ባለፍው ሳምንት የቻይና እና አፍሪካ ንግድ ምክር ቤት ሀላፊ የሆኑት ዲያና ቼን ከሌጎስ ንግድ ምክርቤት ሀላፊዎች ጋር የጋራ ስምምነቱን በተፈራረሙበት ወቅት ቼን እንደተናገሩት፣ ቻይና ለማውጣት ያቀደችው የ300 ቢሊየን ዶላር መዋዕለ ንዋይ በሚቀጥሉት ሶስት አመታት ውስጥ በተለያዩ የአፍሪካ ሀገሮች ላይ የሚተገበር ይሆናል።
በርካታ ባለሙያዎች የዚህ አይነት ልማት የሀገር ውስጥ ምርትን የማሳደግ እና ሀገር በቀል የሆኑ የናይጄሪያና የአፍሪካ መለያ ያላቸውን ምርቶች ወደ ውጪ የመላክ አቅምን እንደሚጨምር ተናግረዋል። ቻርልስ ኦኑናጂ በአቡጃ የሚገኘው የቻይና ጥናት ማዕከል ዳይሬክተር ናቸው።
"በሌጎስ ብቻ ሳይሆን በሁሉም የአፍሪካ ሀገራት ነው የሚተገበረው። በቻይና እና በአፍሪካ መሃከል ሊኖር ስለሚችል አዲስ ትብብር ወይይት ሲካሄድ ቆይቷል። በሌጎስ የተካሄደው ስብሰባ፣ በዳካር ተካሂዶ የነበረውና የቻይናው ፕሬዝዳንት የቻይናና የአፍሪካን ትብብር ከፍ ወዳለ ደረጃ ለማሳደግ ዘጠኝ ፕሮግራሞችን ቃል የገቡበት ስብሰባ ተከታይ ነው። ለኔ ይሄ በቻይና እና በአፍሪካ መሃከል ለሚኖረው ትብብር ትልቅ ምዕራፍ ነው።"
ቻይና 30 ቢሊየን ዶላር በሚያወጣ ዋጋ የአፍሪካ ትልቁ የንግድ አጋር በመሆን ዩናይትድ ስቴትስን እና አውሮፖአን አልፋለች። ከአፍሪካ ደግሞ ናይጄሪያ የቻይና ቁጥር አንድ የንግድ አጋር ናት። የአዲሱን ስምምነት ጉዳይ የሚከታተሉ ተንታኞች ወደ አንድ ወገን ያመዘነ ሽርክና ነው ሲሉ ቢተቹትም፣ ኦኑናጂ ስምመንቱ አፍሪካ ከቻይና ጋር ያላትን ንግድ የሚያሻሽል ነው ይላሉ።
"ቻይና ለነዚህ አይነት ቅሬታዎች መልስ ለመስጠት አፍሪካ ገበያዋን በተሻለ ሁኔታ እንድትጠቀም እድሎችን እያመቻቸች ነው። በኔ እይታ በሶስት አመት ውስጥ 300 ቢሊየን ዶላር የሚያወጣ የአፍሪካን ምርት ለማስገባት ያሰበችው እቅድ ብዙ ነገሮችን የሚቀይር ነው።"
የቻይና ባለስልጣናት በአዲሱ ስምምነት መሰረት ቻይና ከአፍሪካ የሚመጡ ምርቶችን የምትቀበልበት ልዩ የኢኮኖሚ ዞን እንደምታቋቁም ይናገራሉ።
የናይጄሪያ የግል ነጋዴዎች ማህበር ፕሬዝዳንት የሆኑት አዴቶኩንቦ ካዮዴ ግን ይህ ስምመንት አፍሪካ ከቻይና ያለባትን ብድር መጠን የበለጠ እንዳያባብሰው ይሰጋሉ።
"ብዙ የአፍሪካ ሀገራት አይናቸውን ጨፍነው የማይወጡት እዳ ውስጥ ገብተዋል። ይሄ በግልፅ የሚታይ ነው ምክንያቱም ከብዙ ሀገራት የወሰዷቸው ተቋማት ሲታይ ብድራቸውን መክፈል የሚያስችል አቅም እንደሌላቸው ያሳያል።"
ካዮዴ ጨምረው ቤይጂንግ አፍሪካ ላይ መዋዕለ ንዋይ እያፈሰሰች ቢሆንም፣ አብዛኛውን ግዜ አፍሪካውያን እራሳቸው ፕሮጀክቶቹን በማስፈፀም ስራ ላይ ስለማይሳተፉ የእውቀት ክፍተት ይፈጠራል ይላሉ።
ይህ የቻይና ስምምነት ስኬት ቻይና እና የአፍሪካ ሀገራት በጋር ያወጧቸዋል ተብሎ የሚጠበቀው የቻይና የንግድ ፖሊሲ ተስማሚነት ላይ እንደሚወሰን ባለሙያዎች ቢያስረዱም ካዮዴ ግን በዚህ አይስማሙም።
"እኛ ከቻይና ጋር ያለን የንግድ ፖሊሲ ምን አይነት ነው? እኔ በናጄሪያ ውስጥ ባለኝ ሙያ ምክንያት የማወቅ ችሎታ ቢኖረኝም፣ እስካሁን ድረስ ናይጄሪያ ከቻይና ጋር ያላትን ፖሊሲ ልቅም አድርጎ የሚያሳይ ምንም አይነት መረጃ አይቼ አላውቅም። ለምሳሌ በበርካታ ቢሊየን ዶላር ስምምነቱ መሰረት የሚመረቱ የሀገር ውስጥ ምርቶችን በምን መልኩ ማበረታታት እንደሚቻል የሚገልፅ ፖሊሲ እንኳን አላየሁም።"
እ.አ.አ ከ2018 አንስቶ የቻይና ባለስልጣናት፣ የቻይናና አፍሪካ ኢኮኖሚ እና ንግድ ኤክስፖ በመካከለኛው ቻይና በሚገኘው ቻንግሻ ከተማ ማካሄድ ጀምረዋል። አላማውም የአፍሪካን ምርቶች በቻይና ገበያ ውስጥ ማስተዋወቅ የሚል ነው።
በርካታ የአፍሪካ ንግዶች በቻይና ገበያ ውስጥ ተቀባይነት ለማግኘት እየሞከሩ ቢሆንም በርካቶች አዲሱ ስምምነት አሁን ያለውን የገበያ ሁኔታ በምን መልኩ እንደሚቀይረው ለማየት እየጠበቁ ነው።