በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ጉተሬዥ ሰላም ለማስፈን የሚያስችል ተጨባጭ ጥረት በመኖሩ ተደስቻለሁ አሉ


ፎቶ ፋይል፦ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሀፊ አንቶኒዮ ጎተሬዥ
ፎቶ ፋይል፦ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሀፊ አንቶኒዮ ጎተሬዥ

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሀፊ አንቶኒዮ ጎተሬዥ በአፍሪካ ህብረት የአፍሪካ ቀንድ መልዕክተኛ ክቡር ኦሊሲንጎ ኦቦሳንጆ በኢትዮጵያ ባለው ግጭት ዙሪያ በመቀሌና በአዲስ አበባ ያደረጉትን ግብኝት ተከትሎ በዛሬው እለት የስልክ ውይይት አድርጌያለሁ ሲሉ ዛሬ ባወጡት መግለጫ አስታወቁ፡፡

ሰላም ለማስፈን የሚያስችል ተጨባጭ ጥረት በመኖሩ ተደስቻለሁ ብለዋል፡፡

"ኦባሳንጆ በኢትዮጵያ መንግሥትና ህወሓት ግጭቱን ለማስወገድ እያደረጉ ስላሉት ጥረት ገለጻ አድርገውልኛል” ያሉት ዋና ጸሀፊው ግጭቱና ጥቃቱ እንዲያበቃ አሁን ፖሊካዊና ዲፕሎማሲያዊ እልባት ለመስጠት የሚያስችል ትክክለኛ እድልና አጋጣሚ ስለመኖሩ ተስፋ ማድረጋቸውን ገልጸዋል፡፡

ጉተሬዥ በመግለጫቸው ከአንድ ዓመት በላይ በመላው ኢትዮጵያና በአካባቢው በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ለጉዳት ከዳረገው ግጭት በኋላ አሁን ሰላም ለማስፈን የሚያስችል ተጨባጭ ጥረት በመኖሩ ተደስቻለሁ ብለዋል፡፡

በአንዳንድ የሰሜን ኢትዮጵያ አካባቢዎች አሁንም የሚካሄደው ውጊያ ለሰላም ሂደቱ መራር ፈተና መሆኑን የገለጹት ዋና ጸሀፊው በሁሉም ወገኖች ዘንድ መተማመን የሚፈጥሩ ጠንካራ እምርጃዎች እየተወሰዱ ነው ብለው ተስፋ ማድረጋቸውን ተናግረዋል፡፡

ጎተሬዥ አሁንም ሰላምን ለማስፈን ትክክለኛው አቅጣጫ ሁሉም ወገኖች ግጭቱን ማቆሙ ያላባቸው መሆኑን ያቀረብኩትን ጥሬዬን እንደገና አቀርባለሁ ብለዋል፡፡

የተባበሩት መንግሥታት ኢትዮጵያ ውስጥ በአገሬው ሰዎች ባለቤትነት የሚመራ ሁሉን አቀፍ ብሄራዊ የሰላም የደህንነትና የእርቅ ሂደትን ለመደገፍ ዝግጁ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብም ሁሉም ወገኖች ለሰላሙ ሂደት በቅንነትና በቁርጠኝነት እንዲሳተፉ የሚያደርገውን ጥረት መቀጠል አለበት ብለዋል፡፡

በአፍሪካው ህብረት እየተመራ ያለው የሰላም ጥረት ትልቅ ተስፋ የሚሰጥ ቢሆንም በጦርነቱ የተጎዱ የተለያዩ አካባቢዎች ያለው የሰብአዊ ቀውስ አሁንም ያሳስበናል ብለዋል፡፡

አሁንም በኢትዮጵያ ውስጥ ሁሉም ወገኖች አገር ውስጥ ያሉትም ሆነ ዓለም አቀፉ ማህበረሰ ለሰብአዊ እርዳታ ተደራሽነት የሚያደርገውን ጥረት እንዲደግፉ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡

XS
SM
MD
LG