ገዥው ብልፅግና ፓርቲ ትላንት የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ስብሰባ አካሂዶ የአመርራ አባላቱ ወደ ጦር ግንባር እንዲዘምቱ አጠቃላይ ውሳኔ አስተላልፎ ነበር።
ይህን ውሳኔ ተከትሎም ትላንት ሰኞ ኅዳር 13/2014 ዓ.ም ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ ወደ ጦር ግንባር እንደሚዘምቱ ባወጡት ጹሑፍ አሳወቁ። ዛሬ ጦር ግንባር ላይ መገኘታቸው ተነግሯል።
በሌላ በኩል የህወሃት ቃል አቀባይ ጌታቸው ረዳ ዛሬ ባወጡት ትዊት የጠቅላይ ሚኒስትሩን ወደ ግንባር የመዝመት ውሳኔ አጣጥለዋል።
የዩናይትድ ስቴትስ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ ልዑክ አምባሳደር ጄፍሪ ፌልትማን ዛሬ በሰጡትና ማምሻውን በደረሰን መግለጫ ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድና ከህወሃት መሪዎች ጋር በቅርቡ ካደረጓቸው ውይይቶች ለግጭቱ መፍትኄ ለመፈለግ ወደ ዲፕሎማሲያዊ መንገድ ለመመለስ ዕድል እንዳለ ተናግረዋል።
እስካሁን ባደረጓቸው ጥረቶች “ግዙፍ” ያሉት ውጤት ማየታቸውን ፌልትማን ገልፀዋል። ይሁን እንጂ የዲፕሎማሲ ጥረቶቹ መሬት ላይ ባሉት ሁኔታዎች ሊዋጡ እንደሚችሉም ሥጋታቸውን ገልፀዋል።
በጉዳዩ ላይ ኔዘርላንድስ የሚገኘው ዓለምአቀፍ የዴሞክራሲና የምርጫ ድጋፍ ኢንስቲትዩት ባልደረባ የሆኑትን የሕግና የፖለቲካ ጉዳዮች ተንታኝ ዶ/ር አደም ከበደ አወልና በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሥነ ጥበብና የዲዛይን ትምህርት ቤት መምህር፤ የኢትዮጵያ ቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተርና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል አቶ አበባው አያሌውን አስተያየት ጠይቀናል።
//ዝርዝር ዘገባውን ከተያያዘው የምስል ፋይል ያዳምጡ//