በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ ወደ ግንባር እንደሚዘምቱ አስታወቁ


የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ/ ፎቶ ፡- የአሜሪካ ድምፅ/
የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ/ ፎቶ ፡- የአሜሪካ ድምፅ/

የመከላከያ ሠራዊት እና ሌሎች የፀጥታ አካላት በቅንጅት “የተለየ” ወዳለው “እርምጃ እንደሚገቡ” ደግሞ የገዥው ብልፅግና ፓርቲ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አመልክቷል ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዛሬ ምሽት ላይ ኢትዮጵያ የሚለውን የነፃነት ስም የማስጠበቅ የታሪክ አደራ አለብን!” በሚል ርዕስ በማኅበራዊ መገናኛ ገፃቸው ላይ ባሠፈሩት ፅሁፍ ከኅዳር 14/2014 ዓ.ም ጀምሮ ወደ ጦር ግንባር እንደሚዘምቱ አስታውቀዋል።

“ከእንግዲህ እኔ መከላከያን በግንባር ሆኜ ለመምራት ከነገ ጅምሮ ወደ ትግሉ ሜዳ እዘምታለሁ” ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ “ለመላው ጥቁር ሕዝቦችና ለኢትዮጵያዊያን” ሲሉ ባስተላለፉት መልዕክት። ሌሎችም ፈለጋቸውን እንዲከተሉ ጥሪ አቅርበዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚሁ ፅሁፋቸው “የውጭና የውስጥ ጠላቶቻችን” ብለው የገለጿቸው ኃይሎች “ተቀናጅተው መዝመታቸውን” ጠቁመው አሁን ኢትዮጵያን ለመታደግ “የመጨረሻውን ፍልሚያ የምናደርግበት ጊዜ ላይ ነን” ብለዋል። “የእኛ መዝመት የሚፈጥረውን ክፍተት ከግንባር የቀሩት የክልልና ፌደራል አመራሮች በሙሉ ዐቅማቸው ይሠራሉ” ሲሉም አክለዋል።

የፓርቲው የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል ዶ/ር ዓለሙ ስሜም “ከፓርቲያችን ፕሬዝዳንት ጀምሮ ወደ ግንባር ሄደን እኛ መስዕዋት ሆነን ኢትዮጵያን ለማዳን ወስነናል” ብለዋል። የፓርቲው የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል እና የመከላከያ ሚኒስትር ዶ/ር አብርሃም በላይ ደግሞ "የመከላከያ ሠራዊትና ሌሎች የፀጥታ አካላት በቅንጅት ተዘጋጅተው ወደተለየ እርምጃ ይገባሉ" ብለዋል። “እርምጃው” ምን እንደሚሆን ግን በዝርዝር አላብራሩም።

በግጭቱ በተሳተፉ አካላት መካከል ላለው ልዩነት “ወታደራዊ አማራጭ መፍትኄ እንደማይሆን” በመግለፅ ዩናይትድ ስቴትስና የመንግሥታቱን ድርጅት ጨምሮ በግጭቱ ውስጥ ያሉ ሁሉ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ተኩስ ለማቆም ለድርድር እንዲቀመጡ ተደጋጋሚ ጥያቄዎችን ቢያደርጉም እስካሁን በተጨባጭ የታየ ለውጥ የለም። ተፋላሚ ኃይሎቹን ወደ ድርድር ጠረጴዛ ለማምጣት የአፍሪካ ኅብረት፣ ዩናይትድ ስቴትስና ሌሎችም አካላት በጥረቶቻቸው እንደቀጠሉ ነው። ይሁን እንጂ ሁለቱም አካላት “ልዩነታቸው ፖለቲካዊ መሆኑንና በፖለቲካዊ ውይይት መፍታት እንደሚቻል በተናጠል መግለፃቸውን ያብራሩት የአፍሪካ ኅብረት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ ልዑክ ኦሉሴጉን ኦባሳንጆ “ለድርድር ጠባብ አማራጭ መኖሩን ጠቅሰው” ይህን ለማድረግ ግን በአስቸኳይ ግጭቱ ሊቆም እንደሚገባ መናገራቸውም ይታወሳል።

ነገር ግን በተቃራኒው ግጭቱ ከመርገብ ይልቅ ይበልጥ ተባብሶ እንደቀጠለ ሲሆን የሚያስከትላቸው ሰብዓዊ ቀውሶችም አይለዋል። ግጭቱ እየተካሄደባቸው ባሉ ሦስት ክልሎች ማለትም በትግራይ፣ በአማራና በአፋር ክልሎች ሰብዓዊ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው ሰዎች ቁጥር ከስምንት ሚሊዮን መብለጡን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ ድጋፍ ማስተባበሪያ ቢሮ ከቀናት በፊት ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

XS
SM
MD
LG